ቀጥታ፡

በ5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ የተገቡ ቃሎችን ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየርና የአህጉሪቱን የጤና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ የጋራ እርምጃ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2019 (ኢዜአ)፦ በ5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ላይ ቃል የተገቡ ጉዳዮችን ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር፣ ሀገራዊ ባለቤትነትን ለማጠናከር እና የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት ለማሳደግ  የጋራ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ገለጹ፡፡

5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

«የአፍሪካ የጤና ደኅንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት የሚደረግ ሽግግር» በሚል መሪ ሐሳብ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የሀገራት መሪዎች፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሕዝብ ጤና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን፤ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞትን መከላከል የአመራር ቀዳሚ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

በጋና በአክራ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ልዩ የጤና ጉባኤ እና በመስከረም ወር በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተደረጉ ውይይቶች፣ የአፍሪካ መሪዎች ለዘላቂ ፋይናንስና ለጤና ሉዓላዊነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውንና በሦስቱ ዜሮዎች ዙሪያ ጠንካራ ውይይት ማካሄዳቸውን ጠቁመዋል።

ሦስቱ ዜሮዎች በቤት ውስጥ የሚከናወን ወሊድን፣ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞትን እንዲሁም ክትባት ያልወሰዱ ሕፃናትን ዜሮ ማድረግ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህ ሦስት ግቦች እርስ በርስ የተሳሰሩና የተቀናጀ ሀገራዊ እርምጃን በመምራት፣ ነባር የጤና ፖሊሲዎችን በማጠናከር እንዲሁም አፈጻጸምን በማሳለጥ የጤና ሥርዓትን የሚያጎለብቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህም በጥቅምት ወር በታንዛኒያ በተካሄደው የዓለም አቀፍ የፓርላማዎች ኅብረት ጉባኤ ላይ ተገኝተው የእናቶችና የሕፃናት ጤናን ለማሻሻል በሚወጡ የሕግ፣ የፋይናንስ እና የቁጥጥር እርምጃዎች ላይ መምከራቸውን አብራርተዋል።

በአፍሪካ የጤና ደኅንነትንና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጉዞ እና የጋራ ግቦችን ለማሳካት እየተሠራ ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ያስጀመሩት የሌማት ትሩፋት እና የሰቆጣ ቃልኪዳን የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እንዲሁም የእናቶችና የሕፃናትን ጤና በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው በመሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስተሩ ለወሰዱት አመራርነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ሁሉም የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት በቤት ውስጥ የሚከናወን ወሊድን፣ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ሞትንና ክትባት ያልወሰዱ ሕፃናትን ዜሮ ማድረግ ላይ ትኩረት በማድረግ ከሀገራዊ የጤና ስትራቴጂያቸው ጋር ሊያቀናጁ ይገባል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም