ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስርና ለአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ትግበራ ውጤታማነት በቁርጠኝነት እየሠራች ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14 /2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስርና ለአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ትግበራ ውጤታማነት በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሃብረቢ ገለጹ።

‘’ የአፍሪካን ወጪ ንግድ በጥራት መገንባት ‘’ በሚል መሪ ሐሳብ የአፍሪካ ንግድ ልማት ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። 

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በትሬድ ማርክ አፍሪካ (TradeMark Africa) ትብብር የተዘጋጀው ይህ ፎረም፣ የአፍሪካን ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ ነው።

በፎረሙ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የልማት አጋሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሃብረቢ እንደገለጹት፣ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና የተቀናጀ የአፍሪካ ገበያ ለመገንባት፣ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋትና ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለቶችን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና አለው። 

በዚህም ኢትዮጵያ በነጻ ንግድ ቀጣናው የሚገኙ አጋጣሚዎችን ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎች ለመለወጥ በትኩረት እየሠራች መሆኗን አስታውቀዋል።

የባቡርና የመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ ቀጣናውን በኃይል የማስተሳሰር ሥራዎች እንዲሁም የአንድ ማዕከል የድንበር ኬላዎች ግንባታን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ትስስር ላይ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶች፤ ኢትዮጵያ ለዕቃዎችና አገልግሎቶች ነጻ ዝውውር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። 

በተጨማሪም ግልጽ፣ ተገማችና ቀልጣፋ የንግድ ምኅዳር ለመፍጠር ሰፊ የሕግ፣ የቁጥጥርና የሪፎርም ሥራዎች እየተተገበሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደጉን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ማሻሻያው ለወጪ ንግድ መስፋፋትና በኢንቨስትመንት ለሚመራ ዕድገት ሰፊ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል። 

በውጭ ምንዛሬ ላይ የተደረገው ማሻሻያም ላኪዎችን ከሚያበረታቱ አሠራሮች ጋር ተዳምሮ የምርት መጠን መጨመርንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ከፍ ያደረጉ ውጤቶችን ማስገኘቱን አብራርተዋል።

የንግድ ምኅዳሩን ምቹ ለማድረግ የዲጂታል ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቁመው፣ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች የንግድ ፈቃድ የማውጣትና የማደስ አገልግሎቶችን በኦንላይን እያገኙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አክለውም የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ የደረጃዎች፣ የፍተሻ፣ የዕውቅና እና የአክሪዲቴሽን ተቋማትን በአንድ ጣሪያ ሥር ያሰባሰበ ዘመናዊ የጥራት መሠረተ ልማት መገንባቱን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም