ኢትዮጵያ የማይበገር እና ራሱን የቻለ የአፍሪካ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ ናት- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የማይበገር እና ራሱን የቻለ የአፍሪካ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ ናት- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 14 /2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የማይበገር እና ራሱን የቻለ የአፍሪካ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው፤ በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር በአዲስ አበባ በተዘጋጀው የCPHIA 2026 ጉባኤ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በመገኘት ንግግር ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባህላችን ሰላምታ የመልካም ጤንነት ምኞት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም መንፈስ የአፍሪካ ህብረት እና የአፍሪካ ሲዲሲ መቀመጫ ወደሆነችው አዲስ አበባ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባላት የሰው ኃይል፣ በሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት፣ በዲጂታል ጤና እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ላይ ኢንቨስት በማድረግ የማይበገር እና ራሱን የቻለ የአፍሪካ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በመደመር እሳቤ በመመራት፣ የጤና መዋቅራችንን በሦስት ዋና ዋና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ዙሪያ መለወጥ ይኖርብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነሱም የሕክምና ልህቀት ማዕከላትን መገንባት፣ የአፍሪካ አምራቾችን ለማብቃት በጋራ ግዥ መፈጸም፣ እንዲሁም በታካሚዎች ጤና ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ጥብቅ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት የምታስተናግደውን የCOP32 ጉባኤ እንዲታደሙ ታዳሚዎቹን በክብር የጋበዙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቀጣይ ዓመት እንገናኝ በማለት መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።