ቀጥታ፡

ሩሲያ የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት ለማጠናከር ያላትን ትብብር እያጠናከረች ነው - ዶ/ር ኦሌግ ኦሌጎቪች ሳላጋይ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2019 (ኢዜአ)፦  ሩሲያ የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት ለማጠናከር ያላትን ትብብር እያጠናከረች መሆኑን የሩሲያ ፌዴሬሽን የመንግሥት ፀሐፊ እና ምክትል የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ኦሌግ ኦሌጎቪች ሳላጋይ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አምስተኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡

ጉባኤው "የአፍሪካ የጤና ደህንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ፅናት የሚደረግ ሽግግር" በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

ይህ ዓመታዊ ጉባኤ የአፍሪካ የፖለቲካ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የሕዝብ ጤና ባለሙያዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች በአህጉሪቷ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የጤና አጀንዳዎች የሚመክሩበት፣ ሳይንሳዊ ዕውቀቶችን የሚለዋወጡበት እንዲሁም አዳዲስ የፈጠራ መፍትሔዎችን የሚያስተዋውቁበት የትብብር ማዕቀፍ ነው።

በተጨማሪም ጉባኤው ትብብርን ለማጠናከር፣ ምርምርን ለማሳደግ እና የማይበገርና በራስ አቅም ላይ የተመረኮዘ የጤና ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ አፍሪካ-መር አካሄዶችን ለማጠናከር ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።

የሩሲያ ፌዴሬሽን የመንግሥት ፀሐፊ እና ምክትል የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ኦሌግ ኦሌጎቪች ሳላጋይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጉባኤው በአፍሪካ አገሮች በሕዝብ ጤና ዘርፍ እውነተኛ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ከሚያስችሉ እጅግ አስፈላጊ ጉዳዮች አንዱ ነው።

ይህም የሕክምና አገልግሎቶችንና የንፅህና መሠረተ ልማቶችን ማሳደግ፣ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት እንዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ ማዋልን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እንደሚያካትት ተናግረዋል።

የሩሲያ ፌዴሬሽን የሕዝብን ጤና በመጠበቅ ረገድ ለአፍሪካ አጋሮቿ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ገልጸው፤ በቅርቡ የተካሄደው ሦስተኛው የሩሲያና አፍሪካ ጉባኤ በዚህ ዘርፍ ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማስፋፋት ትልቅ እድል መፍጠሩን አንስተዋል።

በተለይም ወረርሽኝ፣ በሽታዎችን በመከላከልና በመታገል ረገድ በጣም ቅርብ የሆነ ትብብር መመስረቱን ጠቁመዋል። 

በዚሁ የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ የሚከናወኑት ሁሉን አቀፍ የትብብር ፕሮግራም የሥራ ዘመን እስከ 2029 ድረስ መራዘሙን አመልክተዋል። 

በዚህም ማዕቀፍ የጋራ ሳይንሳዊ ምርምሮች፣ የሥልጠና መርሃ ግብሮችና ተግባራዊ ልምምዶች በመደበኛነት እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።

በአፍሪካ የአደገኛ ተላላፊ በሽታዎች ወረርሽኝ መከሰትን ለመቋቋም ሩሲያ ባለሙያዎችን ያቀፉ ቡድኖች ወደ አፍሪካ እንደምትልክ  ገልጸው፤ በተጨማሪም ተንቀሳቃሽ የላቦራቶሪ መሣሪያዎች፣ ከፍተኛ መጠን ያላቸው መድኃኒቶች፣ የምርመራና የመከላከያ መሣሪያዎች እንደሚቀርቡም ጠቁመዋል።

በሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች ከሁሉም የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች የሕክምና ዘርፍ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከእነዚህም ብዙዎቹ በሩሲያ ታዋቂ የሕክምና ተቋማት የተግባር ሥልጠና የሚያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፤ በምርምር ሥራዎችም በተከታታይ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም