ቀጥታ፡

"ዱሞ" - የካፈቾ ሴቶች የተማጽኖ ዜማ

(በቀደሰ ተክሌ-ከሚዛን አማን ኢዜአ ቅርንጫፍ) 

አንዳች ለጆሮ የሚከብድ ክፉ ወሬ ወይም ያልተለመደ ነገር ሲሰማ ቸር ቸሩን አሰማን ብሎ ለጆሮ መልካም ነገርን መመኘት ከኢትዮጵያውያን ሕይወት ጋር የተቆራኘ መማጸኛ ቃል ነው። 

የካፈቾ ሴቶች አንዳች ያልተለመደ ነገር በአካባቢያቸው ተፈጥሮ በዓይናቸው ቢያዩ አልያም በሌላ ቦታ ተፈጽሞ ከወሬ ነጋሪ በጆሯቸው ቢሰሙ "ቸር ቸሩን አሰማን" ከማለት ያለፈ ተግባር ነው የሚያከናውኑት። 

ለክፉ ቀን መማጸኛ እንዲሆኑ የተሰናዱ ግጥሞችን እየመዘዙ በዜማ ወደ ፈጣሪ ተማጽኖ ያቀርባሉ። ይህ ሥርዓታቸው ደግሞ "ዱሞ" በመባል ይታወቃል።

"ዱሞ" በካፈቾዎች ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጭ ያልተለመደ ክስተት ሲፈጸም ለአብነት ሰዎች አልያም እንስሳት መወለድ ከሚጠበቅባቸው የሰውነት ቅርጽ አልያም የእንስሳነት አካልና ባህርይ ውጭ በተቀላቀለ ማንነት ቢወለድ ለፈጣሪ የተማጽኖ ዜማ ወይም "ታገኔነ ጎንዶ ሾበ" ለማሰማት በ"ዱሞ" አደባባይ የሚሰባሰቡበት ነው።

የክስተቱን ወሬ ቀድማ የሰማች የሰፈሩ ሴት ላልሰሙ ሴቶች በማሰማት ቀነ ቀጠሮ ይዘው በአፋቸው እህል ውሃ ሳይገባ ንጋት ላይ ከሰፈራቸው ጫፍ ሔደው ይሰባሰባሉ። ከበሮ መችዋ ከበሮውን ከተቀመጠበት አጸዳድታ ማንገቻ አመቻችታ ይዛ ትወጣለች።

በ"ዱሞ" ሥነ ሥርዓት ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሴቶች ያገቡም ያላገቡም ይሳተፋሉ። ለሴቶች ብቻ የተለየ የክዋኔ ባህል በመሆኑ ወንዶች አይሳተፉም። አብዛኛው የዱሞ ትርጉም ከወሊድ ጋር የተገናኘ በመሆኑ ወላድ ሴቶች ይሳተፋሉ።

የ"ዱሞ" ዘፈን ከመጀመሩ በፊት ሴቶቹ ከሚያደርጉት ቅድመ ዝግጅት አንዱ ቅጠል በወገባቸው ማገልደም ነው። በወገባቸው ከታጠቁት ሌላ ከጓሮ የቅመማ ቅመም ቅጠሎችና ሌሎችም ሰብስበው በእጃቸው በመያዝ ነው ለ"ዱሞ" ዘፈን የሚወጡት። 

በተቀጣጠሩበት ቦታ ሰዓት ሳያሸራርፉ ሁሉም ከተሰባሰቡ በኋላ ከመካከላቸው አንዷ እየመራች የ"ዱሞ" ዘፈን ታነሳለች። በዋናነት "ታገኔነ ጎንዶ ሾበ" የሚባል የተማጽኖ ዜማ ጎልቶ ይደመጣል። "ኤችዮ ኤችዮ ቦቻ" የሚለውም ሌላው የዱሞ ዘፈን ነው። 

መሪዋ እነዚህን እና ሌሎች ለዱሞ ብቻ የተለዩ ዘፈኖችን ተራ በተራ ስታነሳ ሌሎቹ እየተቀበሉ ክብ ሰርተው ይዘፍናሉ። የሚዘፍኑትም በእጃቸው የጨበጡትን ቅጠላ ቅጠሎች በሁለት እጅ ወደ ላይ ከፍ አድርገው በመያዝ ነው። 

የ"ዱሞ" የዘፈን ጭብጥ በዋናነት የሚያተኩረው ያ ክፉ ነገር እንዳይደገም ልመና ማቅረብ ላይ ነው። ካፈቾዎች እምነት፣ ዘርና ቀለም ሳይለዩ እጅ ለእጅ ተያይዘው በአደባባይ ስለመልካም ነገር ተማጽኖ ወደ ፈጣሪ የሚያቀርቡበት ኩነት ነው።

የ"ዱሞ" ሥነ ሥርዓት ከተጀመረ በኋላ የምትመጣ ሴት ብትኖር እንዲሁ ዘው ብላ አትቀላቀላቸውም። የተጀመረ ዘፈን እስኪያልቅ ዳር ላይ ሆና ተንበርክካ ይቅርታ ትጠይቃለች። ሴቶቹም ዘፈኑን ጋብ አድርገው ምረናሻል ብለው ወደ ዘፈኑ ያስገቧታል።

ሌላው አስገራሚ የዱሞ ትዕይንት የሰፈሩ ሰው ያልሆነች ሴት በሚዘፍኑበት ጎዳና ብትመጣ ዝም ብላ እንድታልፍ አይፈቀድም። ወደዘፋኞቹ ባትገባም ዳር ላይ ሆና ለተወሰነ ደቂቃ እየዘፈነች ቆይታ ሲፈቀድላት ነው መንገዱን የምታልፈው። 

በሰፈራቸው ወሬው ተሰምቶ ዱሞ ያልተወጣ እንደሆነም ሔዳ ተናግራ በሰፈራቸው ይወጣሉ። ይህም አካባቢን የመጠበቅ እሳቤ ያለው ባህላዊ ሂደት ነው።

ወንዶችም ቢሆኑ ከሴቶቹ ፈቃድ እስካለገኙ ድረስ በሚዘፍኑበት ጎዳና እንዲሁ በዘፈቀደ የማለፍ መብቱ የተገደበ ነው። ሌላ መንገድ ካለ በአቋራጭ ማለፍ አልያም ባሉበት መንገድ ከሔዱ ቆም ብሎ ምረንሀል እለፍ እስኪባሉ ድረስ መጠበቅ የግድ ነው። ይህ ያልተጻፈ ሕግ በካፈቾዎች ዘንድ ሲወርድ ሲዋረድ እስከ ዛሬ የደረሰ ለባህል የመታመን ነጸብራቅ ነው።

የ"ዱሞ" ዘፋኞች ዘፈኑን አንድ ቦታ በመቆየት አልያም በመጓዝ ብቻም አይደለም የሚያከናውኑት። አንድ ቦታ የተወሰነ ደቂቃ ደግሞ እልፍ ብለው ሰፋ ያለ የጎዳና አደባባይ ሲያገኙ እዛው እንዲሁ ቆመው እየዘፈኑ እስካሰቡበት ወንዝ ደረስ ይደርሳሉ።

ሲዘፍኑም ከበሮ መችዋ ከመኻል ትሆናለች። ክብ ሰርተው የከበቡ ሴቶች ከተረከዛቸው ብድግ ብድግ እያሉ እግራቸውን ወደ ጎን እያራመዱ ወዝ ባለው እንቅስቃሴ ወይም የራሱ የሆነ ወጥ ቀለም ባለው ውዝዋዜ ዘፈኑን ከሰውነታቸው ጋር ያዋሕዱታል።

ከሰፈራቸው አንደኛው ጫፍ ተነስተው ወደ ሌላኛው ጫፍ አልያም እንደ አመችነቱ ትልቅ ወንዝ እስካለበት እየዘፈኑ ይሔዳሉ።

የካፈቾ ሴቶች ይህን የጋራ ልመና በዜማ የሚያቀርቡት የሰሙት ከተፈጥሯዊ ሁኔታ ያፈነገጠ ክስተት በፈጣሪ ቁጣ የመጣ ነው ብለው ስለሚያምኑ በዚሁ ይለፍ አምላክ ይታረቀን ማለታቸው ነው።  

በተለይ ከወሊድ ጋር የተያያዘ ክስተት ሲሆን "ታገኔነ" ብለው ማርያም ሆይ አስታርቂን የሚል ቀጥተቻ ትርጉም ያለውን ሀረግ በዘፈናቸው ደጋግመው ያነሳሉ። 

በዚህ ሂደት ወንዙ ላይ ሲደርሱ በእጃቸው የያዟቸውን ቅጠላ ቅጠሎች ይጥሉታል። የሚጥሉበት ወንዝ እንዲሁ ይዞ እንዳይቀመጥ ወራጅ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ነው የሚጥሉት። 

በዚህን ጊዜ ክፉ ነገር ከሕይወታቸውና ከመንደራቸው ተጠራርጎ እንዲሔድ እና መልካም መልካሙን ደግሞ ፈጣሪ እንዲያበዛላቸው እርስ በእርስ ይመራረቃሉ። 

ከወንዙ ሲመለሱም ዘፈኑ የሚቀጥል ቢሆንም በዚህ ጊዜ የዜማውም የዘፈኑም ይዘት ይቀየራል። በተስፋ ልቦናቸው ተሞልቶ በጎ ነገር እንደሚደረግላቸው የሚገልጹ ስንኞች ይመዘዛሉ። 

ሲሄዱ ፈጣሪን መማጸነና ልመና ላይ ያተኮረ ዘፈን ሲያዜሞ ቆይተው አሁን ደግሞ ወደደስታ ዘፈን ይሸጋገራሉ። ቅጠሉን እንደጣሉ በአቅራቢያው የሚገኝ ወንድ ካለ ከበሮ ተቀብሎ "ዎሆ ምሽራቻ" የተሰኘ የደስታ ጊዜ ዘፈን እየዘፈኑ ወደ መንደራቸው ይመለሳሉ። 

ቅድም በተጠንቀቅ በተመጠነ ዜማና ግጥም ብቻ ታጥረው ሲዘፍኑ የነበሩ ሴቶች የሙገሳና የአክብሮት መግለጫ ስንኞችን በፈጠራ እየቋጠሩ እንዳሻቸው ይዘፍናሉ።

ዘፋኞቹ ከ"ዱሞ" ደክሟቸው ስለሚመለሱ ሰፈር ውስጥ የቀሩ አረጋውያን እናቶች አልያም በተለያየ ምክንያቶች በዱሞ ያልተገኙ ሴቶች ቡና አፍልተው ይጠብቋቸዋል። የዱሞ ዘፋኞችም በፍቅር ያገኙትን ተቋድሰው እረፍት አድርገው ወደቤታቸው ይበታናሉ።

ይህ የዱሞ ሥነስርአት የካፈቾ ሴቶች በመንደራቸው በአንድ የሚሰባሰቡበት አንዱ አጋጣሚ ነው። የእርስ በእርስ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ ስለ ነገ መምከርን፣ ከክፉ ሥራ ርቆ መኖርን የሚነጋገሩበት፣ በሆነው አዝነው ለቀጣዩ የሚለምኑበት የአደባባይ ኩነት ነው።

እንደ ዱሞ ሁሉ በሀገራችን ውስጥ ባሉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚከወኑ ቱባ ባህላዊ ሁነቶች አሉ። ክዋኔዎቹ  በብሔረሰቦች ዘንድ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ናቸው። ብዙዎቹ የራሳቸው የሆነ በጎ እሴትና ሀገርኛ ቀለም የሚንጸባረቅባቸው ሲሆን ባልተጻፈ የልቦና ሕግ የመመራት ሥርዓት ያላቸው እነዚህ ባህሎች የታማኝነት፣ አንዱ ለሌላው የማሰብና መልካም ተግባርን የማበረታት መሠረት ያላቸው ናቸው። 

ክዋኔዎቹ በሀገር በቀል እውቀት የተቃኙ በመሆኑ ህብረተሰቡ እርስ በእርስ በቀላሉ የሚግባባቸው መድረኮች ናቸው ማለት ይቻላል። በመደመር መንግሥት ለሀገር በቀል እውቀት በተሰጠው ትኩረት እነዚህ ባህላዊ ሀብቶች በጥናት ተደግፈው ወደአደባባይ እንዲወጡና ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ ይገኛል። 

እንደ "ዱሞ" ያለው ለየት ያለ ባህል ደግሞ ለብዙዎች አግራሞትን ከሚፈጥሩ የጥበብ ሥራዎች ውስጥ የሚጠቀስ ነው።
ዱሞ የመማጸኛ ዜማ ከመሆን ባሻገር በውስጡ የአለባበስ ጥበብን፣ የዜማ አጯጯህ ስልትን፣ የወዝዋዜ ቀለምና የዜማ መሳሪያና ሥነ ግጥምን ጭምር የያዘ የኪነ ጥበብ ዘውግ ነው። 

በዚህ የዱሞ ሥርዓት የሰፈሩ ጎበዝ ገጣሚ፣ ጎበዝ ድምጻዊትና ጎበዝ ከበሮ መቺ ተለይታ ትሞገሳለች። ለሌላ ኩነት ዕድል ተሰጥቷት በተሰጥኦዋ ሰፈሩን ታገለግላለች። 

መሰል ኩነቶች ለኪነ ጥበብ ዘርፉ ብቁ የሰው ሀይል ማፍሪያ መንገዶች ሆነው እንደሚያገለግሉም ከሥርዓቱ ዝርዝር ሁኔታ መረዳት ይቻላል። የትናንት በጎውን ከዛሬው ጋር አጣምሮ መጠቀም በራስ ቀለም የመድመቅ ዕድልን ስለሚጨምር ይህን ማጠናከር ያስፈልጋል። ቸር ቸሩን ያሰማን። ሰላም!

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም