ቀጥታ፡

ታላቁ ሩጫ የኢትዮጵያውያንን አንድነትና አብሮነት በተግባር ለዓለም ማኅበረሰብ ያሳየንበት ሁነት ነው - የተሳታፊዎች አስተያየት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/2019 (ኢዜአ)፡- ዛሬ የተካሄደው 26ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያንን አንድነትና አብሮነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተግባር ያሳዩበት ሁነት መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የውድድሩ ተሳታፊዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከአበበ ቢቂላ አንስቶ እስከ ዛሬው ትውልድ ድረስ ድንቅ አትሌቶችን በማፍራት በዓለም አደባባይ በረጅም ርቀት ሩጫ ስሟን በደማቁ አስጽፋለች።ይህ ቀጣይነት ያለው የድል ጉዞ የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ፣ ለአዲሱ ትውልድ ትልቅ የብርታትና የአሸናፊነት መንፈስ ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።

26ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት "ሩጫዬ ቀለሜ" በሚል መሪ ሐሳብ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን ጨምሮ ከ61 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል።

10 ኪሎ ሜትር በሸፈነው በዚህ ውድድር በወንዶች ይስማው ድሉ፣ ታከለ ሞሴ እና ሮባ መርጋ እንዲሁም በሴቶች የኔዋ ንብረት፣ አልማዝ ዮሐንስ እና አለምነሽ ጥላዬ ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት አሸንፈዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሁነቱ ተሳታፊዎች፣ የሩጫ መርሐ ግብሩ በታላቅ ደስታ የተሳተፉበትና 10 ኪሎ ሜትሩን ሮጠው ያጠናቀቁበት መሆኑን ተናግረዋል።

ታላቁ ሩጫ ከተጀመረ አንስቶ በሁሉም መርሐ ግብሮች ላይ መሳተፋቸውን የገለጹት አቶ ሰለሞን አለማየሁ፣ ሁነቱ ሁሉም ተሳታፊዎች በጋራ የሚሮጡበት ልዩ መድረክ መሆኑን አንስተዋል። ይህም ጤናቸውን እንዲፈትሹ ከማስቻሉ ባለፈ የኢትዮጵያውያንን አንድነትና ፍቅር ለዓለም ያሳዩበት መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ዮሴፍ አሰፋ በበኩላቸው፣ ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ በመርሐ ግብሩ መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ መሰል አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ዘውትር በማድረግ ጤናቸውን እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።በመርሐ ግብሩም ሁሉም በደስታና አንድነቱን በሚገልጽ መልኩ መሳተፉን አመልክተዋል።

በመርሐ ግብሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉት ወይዘሮ አስቴር ልቄ፣ "ታላቁ ሩጫ እንዲህ ያምራል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፤ በመርሐ ግብሩ ልዩ ደስታ ስለተሰማኝ 10 ኪሎ ሜትሩን ሮጬ ጨርሻለሁ" ብለዋል።

ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያዊ አንድነትና መተሳሰብ የሚታይበት መሆኑን በመመልከቱ ባለፉት 25 ዙሮች ላይ አለመሳተፉ እንደቆጨው የገለጸው ደግሞ ወጣት በአንተአምላክ አይተናል ነው።

ስፖርት ለጤንነት ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ በሁሉም የታላቁ ሩጫ ዙሮች ላይ መሳተፉን የተናገረው ወጣት ሚክሎድ ግርማ ሲሆን፤ ታዳጊ ዳዊት ፍሥሐ ደግሞ በሩጫው ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉ እንዳስደሰተውና በቀጣይም ለመሳተፍ መነሳሳት እንደፈጠረለት ገልጿል።

#ታላቁሩጫበኢትዮጵያ #አንድነት #አዲስአበባ #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም