ቀጥታ፡

ታላቁ ሩጫ በቀጣይ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ በትኩረት ይሠራል - አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ

አዲስ አበባ፣ህዳር 13/2019 (ኢዜአ)፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በቀጣይ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ የውድድሩ መሥራች አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከአበበ ቢቂላ አንስቶ እስከ ዛሬው ትውልድ ድረስ ድንቅ አትሌቶችን በማፍራት በዓለም አደባባይ በረጅም ርቀት ሩጫ ስሟን በደማቁ አስጽፋለች።

ይህ ቀጣይነት ያለው የድል ጉዞ የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ፣ ለአዲሱ ትውልድ ትልቅ የብርታትና የአሸናፊነት መንፈስ ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።

26ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት "ሩጫዬ ቀለሜ" በሚል መሪ ሐሳብ ከ61 ሺህ በላይ ሰዎች በተሳተፉበት በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል።

10 ኪሎ ሜትር በሸፈነው በዚህ ውድድር በወንዶች ይስማው ድሉ፣ ታከለ ሞሴ እና ሮባ መርጋ እንዲሁም በሴቶች የኔዋ ንብረት፣ አልማዝ ዮሐንስ እና አለምነሽ ጥላዬ ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት አሸንፈዋል።

የውድድሩ መሥራች አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ውድድሩን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፣ ኢትዮጵያ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማዘጋጀት እንደምትችል በተግባር መታየቱን ገልጸዋል።

በዘንድሮው ውድድር ከ61 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች መሳተፋቸውን ጠቁመው፤ ቀደም ሲል ከነበረው አንጻር ዘንድሮ የተሳታፊዎች ቁጥር መጨመሩንና በአደረጃጀትም የተሳካ ሆኖ መከናወኑን ተናግረዋል።

መርሐ ግብሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውና በቀጣይም በዘርፉ ተተኪ ትውልድ ማፍራት ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ገልጸው፤ በዚሁ መሠረት በዘንድሮው ውድድር ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የመጡ ሦስት ሺህ ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።

በውድድሩ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ከውጭ የመጡ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መሳተፋቸውንም አመልክተዋል።

ታላቁ ሩጫ ተተኪዎችን ለማፍራት፣ ሕዝቡን ለማሳተፍና ወደ ስፖርት እንቅስቃሴ ለማስገባት ሲሠራ መቆየቱን የገለጹት አትሌት ኃይሌ፤ ውድድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ለከተማ አስተዳደሩ፣ ለከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

#ታላቁሩጫበኢትዮጵያ #ኃይሌገብረሥላሴ #አትሌቲክስ #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም