ቀጥታ፡

በአምስተኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል

አዲስ አበባ፣ህዳር 13/2019 (ኢዜአ)፡- በአምስተኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል።

በዚህም በዛሬው ዕለት የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ፣ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄሲካ አሉፖ እና የሩዋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ንሴንግዩምቫ አዲስ አበባ ገብተዋል።

መሪዎቹ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ፍሬሕይወት ታምሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ኢትዮጵያ ከነገ ኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል (AICC) የሚካሄደውን 5ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) ታስተናግዳለች።

ከ100 በላይ ከሆኑ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችም በዚህ ታላቅ አህጉራዊ መድረክ ላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር የሚዘጋጀው ይህ ጉባኤ፤ ''የአፍሪካ የጤና ደኅንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነት እና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነት እና የማይበገር አቅም መሸጋገር''በሚል መሪ ሐሳብ ነው የሚካሄደው።

ዓመታዊ ጉባኤው የአፍሪካ የፖለቲካ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የሕዝብ ጤና ባለሙያዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች በአንድ መድረክ ተገናኝተው በአህጉሪቷ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የጤና አጀንዳዎች ላይ የሚመክሩበት፣ ሳይንሳዊ ዕውቀቶችን የሚለዋወጡበት እንዲሁም አዳዲስ የፈጠራ መፍትሔዎችን የሚያስተዋውቁበት የትብብር ማዕቀፍ ነው።

በተጨማሪም ጉባኤው ትብብርን ለማጠናከር፣ ምርምርን ለማሳደግ እና የማይበገርና በራስ አቅም ላይ የተመረኮዘ የጤና ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ አፍሪካ-መር አካሄዶችን ለማጎልበት ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም