ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልና ማከም የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት አከናውናለች - የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ህዳር 13/2019 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልና ማከም የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኗን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የመጀመሪያው የአፍሪካ ቀጣናዊ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ዋና መሥሪያ ቤት ተካሂዷል።

ጉባኤው "ከቃል ኪዳን ወደ አፍሪካ-መር ተግባር፤ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ የጤና ደኅንነት፣ ራስን መቻልንና አይበገሬነትን ማዳበር" በሚል መሪ ሐሳብ ለሁለት ቀናት ነው የተካሄደው።

በዚሁ ወቅት በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የአዕምሮ ጤና ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት አየለ እንደገለጹት፤ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ሲጋራ እንዳይጨስና የአልኮል መጠጦች ማስታወቂያ በመገናኛ ብዙኃን እንዳይተላለፍ የሚከለክል አሠራር ተግባራዊ ተደርጓል። ይህም የሲጋራ ማጨስና የአልኮል መጠጥ አጠቃቀም ላይ መሻሻል እንዲኖር ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከናወነው የኮሪደር ልማትም የኅብረተሰቡን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ባህል በማሳደግ ለጤና አጠባበቅ ጉልህ ፋይዳ ማስገኘቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን መተግበሯና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በብዛት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረጓ የአየር ብክለትን በመቀነስ ለኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ጤናማ ያልሆኑ የታሸጉ ምግቦችን በመቆጣጠር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከልና ለመግታት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው፤ በጉባኤው በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መለየትና እርስ በርስ መማር የሚያስችሉ ውይይቶች መደረጋቸውን ዶክተር ሰላማዊት አብራርተዋል።

የአፍሪካ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ማኅበራት ጥምረትና የምሥራቅ አፍሪካ ጥምረት ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ካውሺክ ራማያ በበኩላቸው፤ በማኅበሩ አማካኝነት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በጋራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም