ታላቁ ሩጫ የስፖርት ቱሪዝምን ከማነቃቃት ባለፈ የኢትዮጵያን ድንቅ እሴቶች በማስተዋወቅ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው - ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ ሩጫ የስፖርት ቱሪዝምን ከማነቃቃት ባለፈ የኢትዮጵያን ድንቅ እሴቶች በማስተዋወቅ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው - ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
አዲስ አበባ፣ህዳር 13/2019 (ኢዜአ)፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝምን ከማነቃቃት ባለፈ የኢትዮጵያን ድንቅ እሴቶች ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።
ኢትዮጵያ የጀግኖች አትሌቶች መፍለቂያ እና የረጅም ርቀት ሩጫ ተምሳሌት ሆና በዓለም አደባባይ ስሟን በደማቁ አስጽፋለች።
ከአበበ ቢቂላ ታሪካዊ ድል አንስቶ እስከ ዛሬው ትውልድ ድረስ፣ ሀገሪቱ በኦሊምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮናዎች ሰንደቅ ዓላማዋን በክብር የሚያውለበልቡ ድንቅ አትሌቶችን በማፍራት ትታወቃለች።
ይህ ቀጣይነት ያለው የአትሌቲክስ የበላይነት፣ የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ ለአዲሱ ትውልድ ትልቅ የብርታትና የአሸናፊነት መንፈስ ምንጭ ሆኗል። ዛሬም ተተኪ ወጣት አትሌቶች የቀደሙትን ጀግኖች ፈለግ በመከተል የኢትዮጵያን የድል ጉዞ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ማስቀጠል ችለዋል።
26ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ "ሩጫዬ ቀለሜ" በሚል መሪ ሐሳብ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሂዷል። በመርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ታላቁ ሩጫ አዲስ አበባ በየዓመቱ የምትደምቅበት ታላቅ ሁነት ነው። በውድድሩ ላይ ከከተማዋ ነዋሪዎች በተጨማሪ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትና ከመላው ሀገሪቱ የተወጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ይህ የሩጫ ውድድር የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ከማስተዋወቅ ባለፈ፣ ሀገሪቱ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ማስተናገድ እንደምትችል በተግባር የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።
በዘንድሮው ሩጫ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ ውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃም ትልቅ እውቅና የሚያሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከታላቁ ሩጫ ጋር በመተባበር ከአዲስ አበባ ባሻገር በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ላይ የጎዳና ላይ ሩጫዎችን በማዘጋጀት ተደራሽነቱን እያሰፋ መሆኑንም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
መድረኩ የስፖርት ቱሪዝምን ከማነቃቃት ባለፈ የኢትዮጵያ ባህልና እሴቶች በስፋት ለዓለም እንዲተዋወቁ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ "ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት ናት ስትባል ቀደምትነቷ በአትሌቲክስም ጭምር መሆኑንና ይህንንም ታሪክና ባህል አስተሳስረን ለዓለም የምንነግርበት ጥሩ መድረካችን ነው" ብለዋል።
አሥር ኪሎ ሜትር በሸፈነው በዚህ ውድድር ከአንድ እስከ ሦስት ለወጡ አትሌቶች የገንዘብና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል።
#ታላቁሩጫበኢትዮጵያ #የስፖርትቱሪዝም #አዲስአበባ #ኢዜአ #ENA