በአዲስ አበባ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማቶች የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ለተተኪ ስፖርተኞች ምቹ መድረክ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማቶች የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ለተተኪ ስፖርተኞች ምቹ መድረክ ሆነዋል
አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/2019 (ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ ከኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማቶች ጎን ለጎን የተገነቡት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ለተተኪ ስፖርተኞች ምቹ መድረክ መፍጠራቸውን ታዳጊ አትሌቶች ገለጹ።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች በተለይም በአትሌቲክስ ስሟ ከፍ ብሎ ከሚጠራ ሀገራት አንዷ ናት።ይህንን ስኬት አስጠብቆ ተተኪ ስፖርተኞችን በብዛትና በጥራት ለማፍራትም የስፖርት መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋት ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር ቆይታ ያደረጉ ታዳጊ አትሌቶች፣ የታላላቅ አትሌቶችን ፈለግ በመከተል የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ለማድረግ ጠንክረው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የ16 ዓመቱ የካራማራ አትሌቲክስ ክለብ ታዳጊ አባል ጌታቸው ምስጋን፣ በራሱ ተነሳሽነት ወደ አትሌቲክስ ልምምድ መግባቱን ጠቅሶ፤ በ800 ሜትር ውድድር ሀገሩን ለማስጠራት ጠንክሮ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
የ17 ዓመቷ የምኒልክ አትሌቲክስ ፕሮጀክት አባል ሳምራዊት ተሰማ በበኩሏ፣ አትሌቲክስ የረጅም ጊዜ ሕልሟ መሆኑንና የተመቻቹት የልምምድ ሥፍራዎች ዓላማዋን ለማሳካት እንዳገዟት አመልክታለች።
ሌላኛው የምኒልክ አትሌቲክስ ፕሮጀክት አባል ታዳጊ ኦብሳ ወርቁ፣ በአዲስ አበባ የተገነቡት የስፖርት ማዘውተሪያዎች በአቅራቢያቸው በሚፈልጉት የስፖርት ዓይነት ልምምድ እንዲያደርጉ ምቹ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግሯል።ባለፈው ዓመት በአዳማ ከተማ በተካሄደ ውድድር አዲስ አበባን ወክሎ መወዳደሩን አስታውሶ፣ በቀጣይ በድሬዳዋ ለሚካሄደው ውድድር ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ጠቅሷል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ አትሌቲክስ ፕሮጀክት አሰልጣኝ ብሻወረድ በቀለ፣ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ታዳጊዎችን በማሰልጠን ከ80 በላይ አትሌቶች የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን እንዲቀላቀሉ መደረጉን ገልጸዋል። ታዳጊዎቹ በሳምንት አራት ጊዜ ሥልጠና እንደሚወስዱና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ላይ የተመሠረተ የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና እንዲላብሱ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርትና ሥልጠና ዳይሬክተር ጎሳዬ ዓለምአየሁ በበኩላቸው፣ በከተማዋ ተተኪ ስፖርተኞችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በከተማዋ በ22 የስፖርት ዓይነቶች ከ21 ሺህ በላይ ታዳጊዎች እየሰለጠኑ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ከእነዚህም ውስጥ 960 ታዳጊዎች በሁለቱም ጾታዎች በ15 ማዕከላት የአትሌቲክስ ሥልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙና በርካቶችም ወደ ስፖርት አካዳሚ፣ ክለቦችና ብሔራዊ ቡድን መሸጋገራቸውን አስታውቀዋል።
#አዲስአበባ #ኮሪደርልማት #አትሌቲክስ #ስፖርት #ኢዜአ #ENA