ቀጥታ፡

የጋምቤላ የዓሳ ሀብት፦ያልተነካው የኢኮኖሚ አቅም

ግዙፍ ወንዞችንና ሰፊ የውሃ አካላትን የታደለችው ጋምቤላ፣ በኢትዮጵያ እምቅ የዓሳ ሀብት በቀዳሚነት የምትጠቀስ ምድር ናት።ይህ የተፈጥሮ ጸጋ በአግባቡ ከለማ ለምግብ ዋስትና፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ለውጭ ንግድ ገቢ ወሳኝ ሞተር ሆኖ ያገለግላል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ቻይና፣ ሕንድና ኢንዶኔዥያ፤ በአፍሪካም እንደ ግብጽና ናይጀሪያ ያሉ ሀገራት የዓሳ ሀብታቸውን በዘመናዊ መንገድ በማልማት ከዘርፉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጡ ይገኛሉ።ኢትዮጵያም ያላትን ሰፊ የውሃ ሀብትና እምቅ የዓሳ አቅም በቴክኖሎጂና በዕውቀት በማገዝ ተመሳሳይ ውጤት የማስመዝገብ ሰፊ ዕድል አላት።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ ባሏት ወንዞች፣ ሐይቆችና ኩሬዎች ውስጥ ወደ 200 የሚጠጉ የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከተፈጥሮ የውሃ አካላትና ከሰው ሠራሽ የዓሳ እርባታ በዓመት እስከ 530 ሺህ ቶን የዓሳ ምርት የማምረት አቅም አላት።በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የውሃ አካላትና የተትረፈረፈ የዓሳ ሀብት ከሚገኝባቸው ክልሎች መካከል ደግሞ የጋምቤላ ክልል በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

የጋምቤላ ምድር ሲታወስ፣ የሞቃታማው አየር ለዛ፣ የባሮ ወንዝ ጸጥታና ለምለሙ ተፈጥሮ ከሁለት የማይረሱ የምግብ ጸጋዎች ጋር ተቆራኝተው በአዕምሮ ይሳላሉ፤ እነሱም ትኩሱ የወንዝ ዓሳ እና ማር የመሰለው የጋምቤላ ማንጎ ናቸው።ለክልሉ እንግዳ የሆነ ሰው እነዚህን ጣዕሞች ቀምሶ ከተመለሰ፣ የጋምቤላ ትዝታው ሁልጊዜም በምላሱ ላይ የሚቀር ጣፋጭ ታሪክ ይሆናል።

ክልሉን አቋርጠው የሚፈሱት ባሮ፣ አኮቦ፣ ጊሎ እና አሌሮ ወንዞች እንዲሁም ሌሎች በርካታ የውሃ አካላት ተራ የውሃ መስመሮች ብቻ አይደሉም፤ ይልቁንም የኢትዮጵያ የውሃ ውስጥ ሕይወት የልብ ትርታዎች ናቸው።

በእነዚህ የውሃ አካላት ከሚገኙት 113 የዓሳ ዝርያዎች ውስጥ 20ዎቹ በገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው መሆናቸው፣ የክልሉን ሀብት ከተፈጥሮ ብዝኃነት ወደ ተጨባጭ የገበያ አቅም የሚያሸጋግር ቁልፍ እውነታ ነው።

በጋምቤላ ወንዞች ውስጥ ከሚገኙትና በገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ካላቸው የዓሳ ዝርያዎች መካከል 'ናይል ፐርች' (Nile Perch) በግዙፍነቱና በግርማ ሞገሱ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል።

ትልቁ የዚህ ዝርያ ዓሳ ከ100 እስከ 150 ኪሎ ግራም ክብደት መመዘኑ፣ የጋምቤላ ወንዞች ምን ያህል ጥልቅና ግዙፍ የውሃ ውስጥ ሕይወትን የሚሸከሙ መሆናቸውን ሕያው ማሳያ ነው።

የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በጋምቤላ ክልል ከሚገኙ ወንዞች፣ ሐይቆችና የተፈጥሮ ኩሬዎች በዓመት ከ17 ሺህ ቶን በላይ የዓሳ ምርት የማግኘት አቅም አለ።

ይሁን እንጂ ይኸው ሀብት ቀደም ባሉት ዓመታት በቂ ትኩረትና ድጋፍ ባለማግኘቱ፣ በቴክኖሎጂ እጥረት፣ በገበያ ትስስር ማነስ እና በመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮች ምክንያት በተፈለገው ደረጃ ሳይለማ ቆይቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ሀገር የዓሳ ሀብት ልማቱን በማዘመን ለምግብ ዋስትና፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል የተቀየሰው ሀገራዊ ግብ፣ በጋምቤላ ክልል አዲስ መነቃቃትና ተስፋ ፈጥሯል።

በተለይም 'የሌማት ትሩፋት' መርሐ ግብር በክልሉ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ጊዜ ወዲህ የዓሳ ምርት መጠን ከዓመት ወደ ዓመት እመርታ እያሳየ መጥቷል።

በክልሉ የዓሳ አስጋሪ ማኅበራትን በስፋት ማደራጀት፣ ዘመናዊ የዓሳ ማስገሪያ ግብዓቶችን፣ የማቀዝቀዣ ሰንሰለቶችን እና የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችን ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም ጠንካራ የገበያ ትስስር መፍጠር፣ የዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት ምርትን በብዛትና በጥራት ለማቅረብ ወሳኝ ምዕራፍ ከፍቷል።

በዚህም ቀደም ሲል በዓመት 400 ቶን ብቻ የነበረው የክልሉ የዓሳ ምርት መጠን በ2018 ዓ.ም ወደ 10 ሺህ ቶን ማደግ ችሏል። ይህም የምርት መጠኑን በ25 እጥፍ ያሳደገ ታሪካዊና ገላጭ ለውጥ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ውጤት ነው።

በቀጣይም በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰፊ የተፈጥሮ የውሃ ሀብት በሰው ሠራሽ የዓሳ እርባታ (Aquaculture) ልማት ማስደገፍ ከተቻለ፣ የዘርፉን እምቅ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ሀገራዊ የምግብ ዋስትናንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በዘላቂነት ማሳደግ እንደሚቻል ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

#ጋምቤላ #የዓሳሀብት #ሌማትትሩፋት #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም