ቀጥታ፡

ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ሆነናል - የአዳማ አርሶ አደሮች

አዳማ፣ህዳር 13/2019 (ኢዜአ)፡- ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ በመስኖ ልማት ተሰማርተው ዓመቱን ሙሉ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን በአዳማ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት፣ የአዳማ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደሮች የውሃ አማራጮችን ተጠቅመው በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ሰብሎችን፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እያመረቱ ይገኛሉ።

ከልማቱ ተሳታፊዎች መካከል የኦላጋ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መገርሳ ቁምቢ፤ ቀደም ሲል ዝናብ ጠብቀው በዓመት አንዴ የሚያካሂዱት እርሻ ከእጅ ወደ አፍ ያለፈ እንዳልነበር ያስታውሳሉ።


አሁን ግን የአዋሽ ወንዝን በመጥለፍ ሸንኮራ አገዳ፣ የበጋ ስንዴ፣ ቲማቲምና በቆሎ በማምረት ገቢያቸው አድጎ ዘመናዊ ቤት መሥራት መቻላቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በኩታ ገጠም ያለሙት የተሻሻለ የፓፓያ ዝርያ ለምርት መድረሱንና መንግሥት ባመቻቸላቸው የገበያ ትስስር ከደላላ ጣልቃ ገብነት ተላቀው የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።


ሌላኛው የአዋሽ መልካሳ ወረዳ አርሶ አደር ቁምቢ ገለታ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በዝናብ የሚያመርቱት ጤፍና በቆሎ ለቤተሰብ ፍጆታ ስለማይበቃ ከሰል በማክሰልና እንጨት በመሸጥ አስቸጋሪ ሕይወት ይገፉ እንደነበር ገልጸዋል።

የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ከሆኑ ወዲህ ግን አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት የምግብ ዋስትናቸውን አረጋግጠው የቆርቆሮ ቤት በመሥራት ኑሯቸው መቀየሩን አስረድተዋል።

የአዳማ ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ቂልጡ፤ አዋሽ ወንዝን በመጥለፍ፣ ምንጮችን በማጎልበትና የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን በመጠቀም አርሶ አደሩ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲያመርት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።


በዘንድሮው የበጋ መስኖ ብቻ 17 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ፣ ቲማቲም፣ ፓፓያ፣ ሸንኮራ አገዳና ሌሎች ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንና አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ኃላፊው አክለዋል።


#መስኖልማት #ግብርና #አዳማ #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም