የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀምራል።
በዕለቱ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከድሬዳዋ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የወቅቱ ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ12 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማን ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 14ተኛ ደረጃ ይዟል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማ በሁሉም ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።
የወቅቱ ሻምፒዮን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን ውስዷል።
ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል።
በሌሎች መርሐ ግብሮች ልደታ ክፍለ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ከረፋዱ አራት ሰዓት፣ ሸገር ከተማ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አዳማ ከተማ ከይርጋጨፌ ቡና በወንጂ ስታዲየም እና ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ከቦሌ ክፍለ ከተማ በማዕከሉ ሜዳ በተመሳሳይ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት እስከ ነገ ይቆያል።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የሸገር ከተማዋ ማርታ ወልዴ እና የመቻሏ ቱሪስት ለማ በተመሳሳይ አራት ግቦች እየመሩ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ እጸገነት ግርማ እና የጉለሌ ክፍለ ከተማዋ ሲርያ ተሾመ በተመሳሳይ ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ይከተላሉ።