የሊጉ መሪ ነገሌ አርሲ ከጋሞ ጨንቻ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ነገሌ አርሲ ከጋሞ ጨንቻ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።
በዕለቱ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።ከቀኑ 10 ሰዓት ነገሌ አርሲ ከጋሞ ጨንቻ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ነገሌ አርሲ በ11 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አዲስ አዳጊው ጋሞ ጨንቻ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃ ይዟል።
ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ድል የቀናው ነገሌ አርሲ ካሸነፈ መሪነቱን ያጠናክራል።
በአንጻሩ ጋሞ ጨንቻ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ይጫወታል። ጋሞ ጨንቻ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አለው።
በሌላኛው መርሐ ግብር ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያለው ፋሲል ከነማ በሶስት ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስምንት ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ፋሲል ከነማ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል። ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀላባ ከተማን ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሰባት ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። አዲስ አዳጊው ሀላባ ከተማ በስምንት ነጥብ 7ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በአምስተኛ ሳምንት ሀላባ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 2 ለ 1 ሲረታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።
ሀላባ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።