ቀጥታ፡

​​​​​​​በመደመር እሳቤ ለቀዳማዊ ልጅነት የተሰጠው ልዩ ትኩረት የትውልድ ግንባታንና ብልጽግናን እውን የማድረግ ራዕይን የሚያጸና ነው - ዶክተር መሠረት ዘላለም

አዲስ አበባ፣ህዳር 13/2019 (ኢዜአ)፡- በመደመር እሳቤ ለቀዳማዊ ልጅነት የተሰጠው ልዩ ትኩረት የትውልድ ግንባታን እና ብልጽግናን እውን የማድረግ ራዕይን የሚያጸና መሆኑን የአፍሪካ የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ማዕከል ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር መሠረት ዘላለም ገለጹ።

ዶክተር መሠረት ዘላለም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመንግሥት ደረጃ ከሚነደፉ የፖሊሲ ማዕቀፎችና ከሚወጡ ሕጎች ጀምሮ ያሉ አውዶች ትውልድን ማዕከል ያደረጉና ነገን የተሻለ የሚያደርጉ ሥራዎችን ለመሥራት ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ይህም በመደመር እሳቤ ውስጥ የትውልድ ግንባታን እና የነገን ብልጽግና መሠረት የማስያዝ ራዕይን የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል።

የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ለአንድ ሀገር ነገ ተስፋ ሰጪ ትውልድን ለማፍራት፣ የዜጎችን ስብዕና ለመገንባት እንዲሁም የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ መሠረት መሆኑን ጠቁመው፤ ዘርፉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ያገኘበት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት ሥራ፣ የሥርዓተ ምግብና የሌማት ትሩፋት ተግባራት፣ እንዲሁም የእናቶችንና የሕፃናትን ሞት ለመቀነስና ጤናቸውን ለማሻሻል የተከናወኑ ሥራዎች የትውልድ ግንባታ ጥረቶች አካል መሆናቸውን አብራርተዋል።

ማዕከሉ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማም በአዲስ አበባ የተገኙ ተሞክሮዎችን በከተማዋ ብቻ ሳይገድቡ ለሌሎች ክልሎች፣ ከተሞች እንዲሁም ለአፍሪካ ሀገራት ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከተማን ለሕፃናት ምቹ ከማድረግ አንጻር አዲስ አበባ ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለአህጉሩና ለዓለም ተምሳሌት መሆኗን ጠቅሰው፤ ይህም በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቀዳማዊ ልጅነት መድረክ ላይ በሰፊው መታየቱን አስታውሰዋል።

መንግሥት ከጽንስ ጀምሮ እስከ ስድስት ዓመት ዕድሜ ላሉ ሕፃናት አካላዊ፣ አዕምሯዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ዕድገት መሠረት የሚጥለውን የቀዳማዊ ልጅነት ልማት መርሐ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል።

መርሐ ግብሩ የተመጣጠነ ምግብ፣ ጤና እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት አገልግሎቶችን በማቀናጀት ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ የመፍጠር ዓላማ ያነገበ ነው።

በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች የሚገኙ ሕፃናት እኩል የዕድገት ዕድል እንዲያገኙ በመንግሥትና በባለድርሻ አካላት ትብብር በስፋት እየተሠራበት ይገኛል።

#ቀዳማዊልጅነት #የትውልድግንባታ #መደመር #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም