በጤናው ዘርፍ የተደረገው የፖሊሲ እና የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያ ኢትዮጵያን በመድኃኒት ምርት ቀዳሚዋ የአፍሪካ ሀገር አድርጓታል - ዶክተር ታደሰ ተፈሪ - ኢዜአ አማርኛ
በጤናው ዘርፍ የተደረገው የፖሊሲ እና የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያ ኢትዮጵያን በመድኃኒት ምርት ቀዳሚዋ የአፍሪካ ሀገር አድርጓታል - ዶክተር ታደሰ ተፈሪ
አዲስ አበባ፣ ኅዳር 13/2019 (ኢዜአ)፡- በጤናው ዘርፍ የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉ እና ጠንካራ የአሠራር ሥርዓት መገንባቱ ኢትዮጵያን በመድኃኒት ምርት ቀዳሚዋ የአፍሪካ ሀገር እንድትሆን ማስቻሉን የኢትዮጵያ መድኃኒትና ሕክምና መገልገያ አምራቾች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የጤና ፖሊሲን በማሻሻል የመድኃኒት አቅርቦቱን ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅና ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ሰፋፊ ሥራዎች ተከናውነዋል። በዚህም በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት ድርሻን ከስምንት በመቶ ወደ 46 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል።
የኢትዮጵያ መድኃኒትና ሕክምና መገልገያ አምራቾች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል። ባለፉት ዓመታት የማክሮ ኢኮኖሚውን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ ተግባራዊ የተደረጉ የፖሊሲና መሰል ማሻሻያዎች የሀገር ውስጥ መድኃኒት ምርታማነትን ማሳደጋቸውን አስረድተዋል
።
የጤና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ሂደት የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ዋነኛው ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ በቅርቡ በአፍሪካ በውስጥ አቅም የሚመረት የመድኃኒት አቅርቦትና ሽፋንን በሚመለከት ሰፊ ጥናት መካሄዱን ጠቁመዋል።
በዘርፉ ስድስት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮችን የዳሰሰው ጥናቱ፤ የመድኃኒት ገበያ ተደራሽነት፣ ለሀገር ውስጥ አምራቾች የተፈጠረ ምቹ ምኅዳር፣ የታክስ ማበረታቻ፣ የዋጋ ደረጃ ተመን እና የተቆጣጣሪ ተቋማት የአሠራር ሥርዓት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ስትወዳደር 88 በመቶ በማስመዝገብ የተሻለ አፈጻጸም እንዳላት በጥናቱ መረጋገጡን አብራርተዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ተግባራዊ እያደረገች ያለው ፖሊሲ ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚውን ሥፍራ እንድትይዝ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን በተግባር ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግሥት ፖሊሲ ከማውጣት ባሻገር ለተግባራዊነቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ታደሰ፤ ከአራት ዓመት በፊት በተገላባጭ ፈንድ ከሚገዙ መድኃኒቶች ውስጥ ስምንት በመቶ ብቻ ከሀገር ውስጥ አምራቾች ይቀርብ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በተከናወኑ የማሻሻያ ሥራዎች አቅርቦቱ ወደ 46 በመቶ ማደጉን አመልክተዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በየዓመቱ በግዢ በሚያስገባቸው መድኃኒቶች ዙሪያ ከማኅበሩ ጋር ጥልቅ ውይይትና ልየታ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ይህ አሠራር የሀገር ውስጥ አቅርቦት አቅምን ለመፈተሽ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
አሠራሩ ፍትሐዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ሀገሪቱ በመድኃኒት ግዢ ምክንያት አላስፈላጊ የውጭ ምንዛሪ ወጪ እንዳታወጣ የሚረዳ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅትም 110 የመድኃኒት ዓይነቶችን በሀገር ውስጥ አምራቾች የመሸፈን አቅም ላይ መደረሱን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
#ጤና #የመድኃኒትምርት #ኢትዮጵያ #ኢዜአ #ENA