የምርት ጥራትን ማስጠበቅ የገበያ ተፈላጊነትን ማሳደግና የብሔራዊ ክብር መገለጫም ጭምር ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የምርት ጥራትን ማስጠበቅ የገበያ ተፈላጊነትን ማሳደግና የብሔራዊ ክብር መገለጫም ጭምር ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ ፣ህዳር 12/2019 (ኢዜአ)፦በጥራት ማምረትና ለገበያ ማቅረብ የምርት ተፈላጊነት መጨመርን ማመላከት ብቻ ሳይሆን የብሔራዊ ክብር መገለጫም ጭምር ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት እና የብሔራዊ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
13ኛ ዙር ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ስነ ስርዓት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሀብረቢ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የ13ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ተወዳዳሪዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት እና የጥራት ሽልማት ድርጅቱ የበላይ ጠባቂ ታዬ አጽቀ ሥላሴ፤ በጥራት ማምረትና ለገበያ ማቅረብ የምርት ተፈላጊነት መጨመር ብቻ ሳይሆን የብሔራዊ ክብር መገለጫም ጭምር ነው ብለዋል።
ዛሬ በጥራት ሽልማት ውድድር ላይ አሸናፊ በመሆን የተለያዩ የደረጃ ሽልማቶችን ላገኛችሁ ተወዳዳሪ ድርጅቶች በሙሉ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
የዛሬ ተሸላሚዎች አቋራጩን መንገድ ሳይሆን ምናልባትም ቀጥተኛውንና አድካሚውን መንገድ መርጣችሁና ተከትላችሁ፣ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ባለው የመመዘኛ መስፈርትና የምዘና ሂደት ውስጥ አልፋችሁ እዚህ በመድረሳችሁ ታላቅ ስኬት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ስኬታችሁ በአገልግሎትና በምርት ጥራት ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ በመረዳት ውጤታማነታችሁን በሦስት ዋና ፍሬዎች ሊገለጥ የሚችል ነው ብለዋል።
እነርሱም ለተገልጋዮቻችሁም ሆነ ለደንበኞቻችሁ የምታቀርቡት ትምህርትም ሆነ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀና አስተማማኝ መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ መቻላችሁ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሁለተኛው የተቋማችሁ አመራሮችና ሰራተኞች የድምር ልፋት ፍሬ ማፍራቱንና ይህም በተቋማችሁ እንድትኮሩና የበለጠ ለመትጋት የሞራል ስንቅ የሚሰጣችሁ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።
ሦስተኛውና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገትና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት ለሚደረገው እርምጃ የእናንተ ስኬት ወሳኝ አቅምና ጉልበት መሆኑን በርግጥ ማስመስከራችሁ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነትና ዘላቂ ብልጽግና ዋናው መሠረት ጠንካራ የሆኑ የመንግሥትና የግል ተቋማትን መገንባት መቻል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚህም መንግሥት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ምርቶች የዓለም አቀፍ የልህቀትና የተወዳዳሪነት መለያ እንዲሆኑ ለማብቃት ሰፊ ዕቅድ ተነድፎ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
መንግሥት ምርትና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ ከሚያደርገው ጥረት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ምርቶች የዓለም አቀፍ የልህቀትና የተወዳዳሪነት መለያ እንዲሆኑ ለማብቃት ሰፊ ዕቅድ ተነድፎ በተግባር እየዋለ ነው ብለዋል።
ለዚህ ትልቁ አብነት ሁላችሁም እንደምታውቁት መንግሥት ከ8.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የገነባውና በአፍሪካ ተጠቃሽ የሆነው የኢትዮጵያ የጥራት መንደር አንደኛው መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ተቋም የጥራት መለኪያ የሆኑ መንግሥታዊ ተቋማትን በአንድ በማሰባሰብ ፈጣንና ቀልጣፋ የተማከለ አገልግሎት ወይም «ዋን ስቶፕ ሰርቪስ» እንዲሰጡ አስችሏል ነው ያሉት።
የንግድና የኢንቨስትመንት ደረጃችንን ከፍ ከማድረጉም ባሻገር የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትልቅ አቅም ፈጥሯል ነው ያሉት።