ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጥራት የማንደራደርበት ቁልፍ ጉዳይ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጥራት የማንደራደርበት ቁልፍ ጉዳይ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ኅዳር 12/2019 (ኢዜአ) ፦ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጉዞ ጥራት የማንደራደርበት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ለ13ኛ ጊዜ የተካሄደው ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ሥነ-ሥርዓት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ያለ ጥራት የሚታሰብ ዕድገት አለመኖሩን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመሆኑም ምርትና አገልግሎቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በሚያደርግ የጥራት ልክ ማቅረብ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግሥት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ አቅም አቀናጅቶ በመጠቀም በሁሉም ዘርፎች የጥራት መሠረተ ልማቶችን በመገንባትና የጥራት ባህልን በማስረጽ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በሀገሪቱ የጥራት ግንዛቤን ለማሳደግና በምርትና አገልግሎት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተቋማትን ለማበረታታት በየዓመቱ የሚያከናውነው ብሔራዊ የጥራት ሽልማት መርሐ ግብር ለሀገራዊ ግብ ስኬት ትልቅ አቅም የሚፈጥርና የሚበረታታ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።