በአዲስ አበባ ጤናማ ከባቢን በመገንባት ሕጻናት በዕውቀትና ሥነ-ምግባር ታንጸው የሚያድጉበት ምኅዳር ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ጤናማ ከባቢን በመገንባት ሕጻናት በዕውቀትና ሥነ-ምግባር ታንጸው የሚያድጉበት ምኅዳር ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2019 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ጤናማ ከባቢን በመገንባት ሕጻናት በዕውቀትና ሥነ-ምግባር ታንጸው የሚያድጉበት ምኅዳር መፈጠሩን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር ገለጹ።
አብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ከፖላንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር “ከቃላት ባሻገር ያሉ ታሪኮች” የተሰኘ የፖላንድ ሕጻናት መጻሕፍት ሥዕላዊ መግለጫዎችን ያካተተ ኤግዚቢሽን አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት፤ አዲስ አበባ ሕጻናት ጤናቸው ተጠብቆ በዕውቀትና በሥነ ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ በማድረግ በኩል ሰፋፊ ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማቶች የሕጻናት ማንበቢያን፣ መጫወቻዎችን፣ ሥዕል መለማመጃ ሥፍራዎችን አካተው እንዲገነቡ መደረጋቸው ለልጆች ጤናማ ዕድገት የተሰጠውን ትልቅ ትኩረት ያሳያል ብለዋል።
የፖላንድ ሕጻናት መጻሕፍት ሥዕላዊ መግለጫ ኤግዚቢሽን በቀጣይ ከሕጻናትና ከቤተ መጽሐፍት ጋር በጋራ ለምንሠራቸው ሥራዎች አብረውን እንዲሠሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ያላቸውን የመማር ማስተማር ልምድ በመጻሕፍትም ሆነ በቴክኖሎጂ ለእኛ በማካፈል በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና የባህል ልውውጥ ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
የኪነ ጥበብ ዘርፉን በማነቃቃት ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ የሥዕል ክህሎታቸውን ማዳበር እንዲችሉ መነቃቃት እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የፖላንድ አምባሳደር ኢሎና ኮርቹት በዚህ ወቅት፤ ኤግዚቢሽኑ ትላንት የተከበረውን የዓለም ሕጻናት ቀን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
የዓለም ሕጻናት ቀን ሕዳር 11 ቀን 1982 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን የጸደቀበት ቀን መሆኑንም አስታውሰዋል።
በዚህም ሕጻናት ደህንነቱ የተጠበቀ መኖሪያና ጥራት ያለው ትምህርት የማግኘት፣ እንዲሁም የጤና ክብካቤ፣ የመጫወትና የራስን ሐሳብ በነጻነት የመግለጽ መብቶች እንዳሏቸው አንስተዋል።
ሕጻናት ፊደል ከመለየታቸው በፊት ሥዕሎች የመጀመሪያ ቋንቋቸው በመሆን እንደሚያገለግሉ ጠቁመዋል።
ምናባዊ ዕይታን በማጎልበትና ገጸ ባሕሪያትን ሕያው በማድረግ በኩልም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው አስገንዝበዋል።
ኤግዚቢሽኑም የፖላንድና ኢትዮጵያን ትብብር ከማጠናከር ባለፈ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያንና ሰዓሊያን በመጻሕፍቶቻቸው ለሥዕላዊ መግለጫዎች እኩል ወይም የላቀ ቦታ እንዲሰጡ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አለም ከበደ፤ ቤተ-መጻሕፍቱ ማንበብ ከጀመሩ ትናንሽ ሕጻናት ጀምሮ እስከ አዋቂዎች ድረስ የሚገለገሉበት የዕውቀትና ጥበብ ማዕከል ነው ብለዋል።
በዚህም ልጆች የሚያነቧቸው መጻሕፍት እንዳሉ ጠቁመው፤ ኤግዚቢሽኑ ልጆች ተመልክተው ሐሳብን በሥዕል የመግለጽ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያግዛል ነው ያሉት።