ቀጥታ፡

በአፍሪካ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚከሰት ሞትን ለመግታት የተገቡ ቃል ኪዳኖችን ወደ ተግባር መለወጥ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2019(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚከሰት ሞትን ለመግታት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ቃል ኪዳኖችን ወደ ተጨባጭ ተግባር መለወጥና የሀገር ውስጥ የገንዘብ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ የዘርፉ የሲቪል ማኅበረሰብ ጥምረት አመራሮች ገለጹ።

የመጀመሪያው የአፍሪካ ቀጣናዊ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ዋና መሥሪያ ቤት እየተካሄደ ይገኛል።

ጉባኤው “ከቃል ኪዳን ወደ አፍሪካ-መር ተግባር፤ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ የጤና ደህንነት፣ ራስን መቻልን እና አይበገሬነትን ማዳበር” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል።

ይህን ጉባኤ የአፍሪካ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ማኅበራት ጥምረት ከአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከልና ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

በዚህ ወቅት የዓለም አቀፉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጥምረት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኬቲ ዴይን፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 43 ሚሊዮን ሰዎችን ለሞት እንደሚዳርጉ ገልጸዋል።

አሁን የተፈጠረውን ዓለምአቀፍና አህጉራዊ የፖለቲካ ቁርጠኝነት በመጠቀም የሕይወት አድን ተግባራትን ማፋጠን ይገባል ብለዋል።

የጥምረቱና የምሥራቅ አፍሪካ ጥምረት ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ካውሺክ ራማያ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚከሰት ሞትንና የዕድሜ ልክ ክብካቤ የሚሹ ሕሙማን ሕክምና እንዳይቋረጥ አፍሪካ ሥርዓት መገንባት አለባት ብለዋል።

ለዚህም መንግሥታት 15 በመቶ በጀታቸውን ለጤና ዘርፉ ለመመደብ የገቡትን የአቡጃ ቃል ኪዳን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ጤናን በሚጎዱ ምርቶች ላይ የጤና ታክስ በማስቀጠል፣ ቀጣናዊ የመድኃኒት ግዥ አቅምን ማጠናከርና የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት መሠረታዊ መድኃኒቶች እንዲቀርቡ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጥምረት የቦርድ ፕሬዝዳንትና ሰብሳቢ ዶክተር አስቻለው ወርቁ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጫና መቋቋም የአንድ ተቋም ወይም መንግሥት ብቻ አይደለም።

በዚህም የጋራ ትብብርን በማጎልበት ጫናውን መቋቋም የሚያስችል ምኅዳር መገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም