ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ተቋማትና ድርጅቶች ጥራትን ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ተቋማትና ድርጅቶች ጥራትን ማዕከል ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ገለጸ።

ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ሥነ ስርዓት በብሄራዊ ቤተ መንግስት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ታዬ አጽቀስላሴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በመርሃ ግብሩ 71 ድርጅቶች ተወዳድረው 56 ድርጅቶች ለሽልማት በቅተዋል።

ኢትዮጵያን በምርትም ተወዳዳሪ ለማድረግና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ጥራት ወሳኝ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ለዚህም ጥራትን ማዕከል አድርገው የሚሰሩ ጠንካራ ተቋማት አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ምርትን በስፋት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ተስፋፍተዋል፣ ለምርት የሚሆኑ መሰረተ ልማቶችም ተሟልተዋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቀጣዩ የቤት ስራ በጥራት ተወዳዳሪ መሆኑን ብለዋል።

ለዚህም ኢንዱስትሪውን የሚመራው የሰው ሃይል ብቃት እና ውጤታማነትን ማሳደግ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል። የምርትና አገልግሎት ውጤታማነት መለኪያው አንዱ መንገድ የዜጎች እርካታ መሆኑን ገልጸው፤ ተቋማት እና ድርጅቶች ጥራት የማሰቢያ መንገዳቸው ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ አባል እና የዳኞች ጉባኤ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ በበኩላቸው፤ ውድድሩ ሽልማት መስጠት ብቻ ሳይሆን የጥራት ባህል በኢትዮጵያ እንዲጎለብት ያለመ ነው ብለዋል።

አንዱ ከሌላው ምርጥ ተሞክሮዎችን እንዲማር ማስቻል ሌላው የውድድሩ ግብ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም