ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና ደኅንነቷን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር የሚያስችል ቁመና አላት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2019(ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና ደኅንነቷን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር የሚያስችል ቁመና ላይ ትገኛለች ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ቢረሳው ሽፈራው ገለጹ፡፡

ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሠራዊት ማኅበር በኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ዙሪያ ከምሁራን ጋር የፓናል ውይይት አካሂዷል።

የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ቢረሳው ሽፈራው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና ደኅንነቷን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር የሚያስችል ቁመና ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ለአካባቢውና ለቀጣናው ሰላምና ደኅንነት ዋስትና የሚሆን አቅም መገንባቷንም ነው የተናገሩት

የኢትዮጵያ በቀጣናው መኖር ለጎረቤት ሀገራትና ለዓለምአቀፍ የንግድ መስመር መረጋጋት ዋስትና እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሠራዊት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር የምትችለው የባሕር በር ባለቤትነቷን ስታረጋግጥ ነው።

የቀድሞው የሠራዊት አባላት፣ የኢትዮጵያን የባሕር በር በማስመለሱ ሂደት ከመንግሥትና ከሕዝብ ጎን እንደሚቆሙ አመልክተዋል።

ስለሆነም ሁሉም ሀገርንና የመከላከያ ሠራዊቱን መደገፍ እንደሚገባው ጠቁመው፤ የማኅበሩ ዓላማም ይኸው መሆኑን ተናግረዋል።

ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሠራዊት ማህበር ሥራ አስፈጻሚና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ መቶ አለቃ ታሪኩ በቀለ፤ የባሕር በር አጀንዳ ሁሌም በውስጣቸው ይመላለስ እንደነበር አውስተዋል።

መቶ አለቃ ታሪኩ እንደገለጹት፤ የባሕር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ዝግጁ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም