ቀጥታ፡

ወላጆች ህጻናት ልጆችን በማስከተብ ለፖሊዮ መከላከል ዘመቻ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

ጉደር ህዳር 12/2019 (ኢዜአ)  ወላጆች ህጻናት ልጆችን የፖሊዮ መከላከያ ክትባት በማስከተብ  ከበሽታው ለመታደግ ለሚካሄደው ዘመቻ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ አሳሰበ።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ማስጀመሪያ ፕሮግራም በማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን ጉደር ከተማ  ዛሬ ተጀምሯል።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ  ምክትል ኃላፊ  አቶ ደረጀ አብደና በወቅቱ አንደተናገሩት፥በክልሉ ከዛሬ ጀምሮ በዘመቻ የሚሰጠው የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት ተደራሽ ይደረጋል።



የፖሊዮ ቫይረስ  ለሞት ጭምር የሚዳርግ በመሆኑ መከላከያ ክትባቱ  ለተከታታይ ጊዜያት በዘመቻ በተቀናጀ መልኩ እየተሰጠ መሆኑን  ገልፀዋል።

በመሆኑም ወላጆች ህጻናት ልጆችን  በማስከተብ ለዘመቻው ስኬታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በክትባት ዘመቻው ላይ ከ35  ሺህ በላይ የጤና ባለሞያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች መሰማራታቸውን አስታውቀዋል።

የማእክላዊ ኦሮሚያ ዞን ጤና ፅህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ዶክተር  አራርሳ ሁሪሳ  በበኩላቸው፥ ክትባቱ ቤት ለቤት  እንደሚሰጥ ጠቁመው ህብረተሰቡ ህጻናት ልጆችን በማስከተብ ሀላፊነቱን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።


 

መንግስት መከላከልንና አክሞ የማዳን የጤና ፖሊሲን እየተከተለ መሆኑን አስታውሰው  የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻም  በሽታውን ቅድሚያ ለመከላከል ምትክ የለሽ መሆኑን አስረድተዋል።

በክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ በክልሉ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ ባለድርሻ አካላት፣ አባ ገዳዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም