ቀጥታ፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አስደናቂ የምህንድስና ጥበብ የተገለጠበት የኢትዮጵያና የአፍሪካ የኃይል ዘርፍ ልማት አኩሪ ስኬት ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2019(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አስደናቂ የምህንድስና ጥበብ የተገለጠበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገትና ቀጣናዊ የኃይል ትብብር አስፈላጊ ምዕራፍ መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ካውንስል ፕሬዝዳንትና የልዑካን መሪ ማይክል ፍሮማን አስታወቁ።

የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ካውንስል (CFR) ልዑካን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዛሬ ጎብኝቷል።

የውጭ ግንኙነት ካውንስል ፕሬዚዳንትና የልዑካን መሪ ማይክል ፍሮማን ጉብኝቱን በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ፤ የሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስፋት፣ ቅልጥፍናና አስፈላጊነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ያደረጉት ከፍተኛ የጊዜ፣ የገንዘብና የክህሎት ኢንቨስትመንት ለሀገራቸው ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አስደናቂ የምህንድስና ጥበብ የተገለጠበት፣ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገትና ለቀጣናዊ የኃይል ትብብር አስፈላጊ ምዕራፍ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአፍሪካ አስተማማኝና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማስፋፋት አስፈላጊ የልማት አቅጣጫ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በአህጉሪቷ ከሚኖረው ሕዝብ ከፍተኛ ድርሻ አሁንም አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንደሌለውም ጠቁመዋል።

በአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ተጀምሮና በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የቀጠለውን የ“ፓወር አፍሪካ” ተነሳሽነት የአህጉሪቱን የኃይል አቅርቦት ለማሟላት እንደሚያግዝ አንስተዋል።

የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን የኢንዱስትሪ ልማት አቅም ለማሳደግም አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሌላኛው የልዑካኑ አባል ማሄሽ ኬ. ኮቴቻ በበኩላቸው፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በመጎብኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የውሃ ኃይል ታዳሽ የኃይል ምንጭ በመሆኑ ያለውን አስፈላጊነት በማጉላት፣ ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ፍጆታም ሆነ ለሰፊው ቀጣና ንጹህ ኃይል በማመንጨት ላይ ያደረገችውን ትኩረት አድንቀዋል።

በተጨማሪም ከኢትዮጵያ የሚመነጨውን ኤሌክትሪክ በመግዛት ጎረቤት ሀገራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሌላኛው የልዑካን ቡድኑ አባል ኬቨን ኪንሴላ፤ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የተንጸባረቀው ድንቅ የምህንድስና ጥበብ የኢትዮጵያውያንን ችሎታ፣ ቁርጠኝነትና ትጋት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ ዘመናዊ ኢንዱስትሪዎችን፣ ቤተሰቦችንና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ ከፍተኛ መጠን ያለው ኤሌክትሪክ የማቅረብ አቅም እንዳለውም መገንዘባቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሌኛዋ የልዑካን ቡድኑ አባል ሚሼል ጋቪን በበኩላቸው፣ የሕዳሴ ግድብን በመጎብኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በውሃ ሀብት ላይ የሚገነባ የታዳሽ ኃይል ልማት ለአካባቢና ሥነ-ምህዳር ደህንነት ጉልህ ፋይዳ ያለው ዓለም አቀፍ የልማት ተነሳሽነት መሆኑን ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አስደናቂ የግንባታ ጥበብም ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባሻገር ለቀጣናው ሀገራት ንጹህ ኃይል በማቅረብ የኢኮኖሚ ትብብርን እንደሚያጠናክር አንስተዋል።

በቀጣይም በቀጣናው ውስጥ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በማስፋፋት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያሉት እድሎች ከፍተኛ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የልዑካኑ ቡድን አባላት ትናንት ከገንዘብ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እና ከብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም