ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ዓለም አቀፍ ትብብርን እና ፍትሐዊ የአየር ንብረት ፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ ትሰራለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12 /2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ዓለም አቀፍ ትብብርን እና ፍትሐዊ የአየር ንብረት ፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ አበክራ እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) “ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” በሚል መሪ ሀሳብ በቱርኪዬ አንታሊያ ሲካሄድ ቆይቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ 32ኛውን ጉባኤ (COP32) የማስተናገድ ኃላፊነቷን በይፋ መረከቧን አብስረዋል።

ሚኒስትሩ 31ኛውን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ላስተናገደችው ቱርኪዬና ለኮፕ 31 ፕሬዝዳንት ሙራት ኩሩም፣ እንዲሁም ድርድሮቹን ሲመሩ ለነበሩት አውስትራሊያና የድርድሩ ሊቀመንበር ክሪስ ቦወን ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በማራቶን ሯጮቿ ጥንካሬና ጽናት እንደምትታወቅ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ የአየር ንብረት ጉባኤዎችም እንደ ቅብብሎሽ ሩጫ መሆናቸውን አመላክተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ዱላውን ከኮፕ 31 ስትረከብ ሁሉም ወገኖች ቀጣዩን ምዕራፍ ከአንታሊያ ወደ አዲስ አበባ አብረው እንዲሮጡና የጋራ ቃል ኪዳኖችን ወደ ተግባራዊ እርምጃ እንዲቀይሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጪው የኢትዮጵያ የኮፕ 32 ፕሬዝዳንትነት ተስፋን መመለስ፣ መተማመንን መልሶ መገንባት እና የጋራ እርምጃን ማጠናከር የሚሉ ሦስት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መለየታቸውን አስታውቀዋል።

በባለብዙ ወገን የአየር ንብረት ትብብር ላይ ያለውን እምነት መመለስ የሚቻለው በተግባር ውጤት በማስመዝገብ በመሆኑ፣ የጉባኤው ውሳኔዎች አፈጻጸምን የሚያሳድጉ መሆን እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኮፕ 32 ዋና ራዕይ የአየር ንብረት እርምጃን ከኢኮኖሚ ልማት ጋር አቀናጅቶ ማስኬድ እንደሆነና ሁለቱ ግቦች እርስ በርስ የሚደጋገፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህንን ለማሳካት በተሳታፊ ሀገራት የሚመራ፣ ሁሉን አቀፍና ግልጽነት ያለው አሠራር በመከተል የጋራ መግባባት ለመፍጠር ሁሉንም ወገኖች በማዳመጥ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

በመደመር እሳቤ አማካኝነት ኢትዮጵያ ለሕዝቧና ለመላው የሰው ልጅ ዓለም አቀፋዊ ትስስር እንደምታሳድግ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይህም የሀገራትን ቅድሚያ ትኩረቶች ማክበርና ለመጪው ትውልድ ኃላፊነት መወጣትን መሠረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በኮንቬንሽኑና በፓሪስ ስምምነት ማዕቀፍ የቤሌምን ተልዕኮዎችና የአንታሊያን ውጤቶች በማስቀጠል ሁሉን አቀፍ ድርድሮችን እንደምታመቻችም ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንትነቱ የአየር ንብረት ለውጥን በመቀነስ፣ የዝግጁነት አቅምን በማሳደግ፣ በኪሳራና ውድመት፣ በፍትሐዊ ሽግግርና በግልጽነት ዙሪያ ሚዛናዊ ውጤቶችን ለማምጣት ይሠራል ነው ያሉት።

በተለይም ለአየር ንብረት ፋይናንስ አቅርቦትና ተደራሽነት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ አዲስ አበባ በሳይንሳዊ መረጃዎች ላይ በመመርኮዝ በሚካሄደው የሁለተኛው ዓለም አቀፍ የግምገማ ምዕራፍ ቴክኒካዊ ግምገማ ወሳኝ መድረክ እንደምትሆን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኮፕ 32 የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሰባሰብ አፈጻጸምን የሚያሳድገውን የድርጊት መርሃ ግብር እንደሚያስቀጥል አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ የፕሬዝዳንትነት ኢኒሼቲቮችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና እነዚህም ከሰፊ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ መርሃ ግብር ጋር ተሳስረው እንደሚቀረጹ አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም ሚኒስትሩ ሁሉንም ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ ለመቀበል በጉጉት እንደሚጠብቁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም