ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የጤና ሳይንስ ኮሌጆችን ደረጃ የማሳደግ ሰራ ትኩረት ተሰጥቷል-ቢሮው

ጎንደር ኢዜአ ህዳር 12/2019 ዓ/ም በአማራ ክልል በጤናው ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የጤና ሳይንስ ኮሌጆችን ደረጃ የማሳደግና የማጠናከር ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷል-የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ። 

የጠዳ ከፍተኛ ትምህርት ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ22ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ከ600 በላይ የጤና ባለሙያዎች ዛሬ አስመርቋል።

የቢሮው የሰው ኃብት ዳይሬክተር ወይዘሮ ምንትዋብ መሐሪ እንዳሉት፣ በክልሉ የጤና ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ የጥራት ደረጃ የማሳደግና ተደራሽነትን የማስፋት ሥራ እየተከናወነ ነው። 


 

በጤናው ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራትና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በጤና ሳይንስ ኮሌጆች ላይ የተለያዩ የማስፋፋትና የማጠናከር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በዚህም የደሴ፣ የባሕር ዳር እና የጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጆችን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ጤና ሳይንስ ኮሌጅነት ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው፣ የደብረ ታቦር እና የደብረ ብርሃን ኮሌጆች ደግሞ በመካከለኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። 

የኮሌጆችን ደረጃ ማሳደግ በዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል በብዛትና በጥራት ለማፍራት የሚያስችል መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የጠዳ ከፍተኛ ትምህርት ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ዳይሬክተር ምክትል ዲን አቶ ታደለ ማሩ በበኩላቸው፣ ኮሌጁ በጤናው ዘርፍ የሰው ኃይል አቅርቦትን ለማሳደግና የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት እየሠራ ይገኛል። 


 

በዛሬው ዕለት ለ22ኛ ጊዜ በስድስት የሙያ ዘርፎች ከ600 በላይ የጤና ባለሙያዎችን በዲፕሎማ መርሃ ግብር ማስመረቅ መቻሉን ገልጸዋል። 

ኮሌጁ የዘርፉን የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ በዲግሪ እና በዲፕሎማ በስድስት የትምህርት ዘርፎች ከሁለት ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

በሚድዋይፈሪ ሙያ የተመረቀችው ተማሪ ድንቡሎ አምባው በበኩሏ፣ በሠለጠነችበት የሙያ ዘርፍ ማኅበረሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቷን ገልጻለች።

ሌላው በፋርማሲ ትምህርት ክፍል የተመረቀው ተማሪ መሠረት ሲሳይ እንዳለው፣ ሙያዊ ሥነ ምግባሩን ጠብቆ በማገልገል የተሰጠውን ሕዝባዊ ኃላፊነት ለመወጣት በታማኝነት እንደሚሠራ ተናግሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም