ቀጥታ፡

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩ የዜጎችን የጋራ እሴቶች ለማጠናከር ያስቻለ ነው-አፈጉባኤው

መተማ ኢዜአ ህዳር 12/2019 ዓ/ም የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩ የዜጎችን  የጋራ እሴቶችን በማጠናከር፣ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ማጎልበት ያስቻለ ነው ሲሉ የገንዳ ውኃ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ጋሻው አራጋው ገለፁ።

ለ21ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "በብዝኃነት የደመቀች፣ በምክክር የፀናች ሥልጡን ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ በገንዳ ውኃ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የገንዳ ውኃ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ጋሻው አራጋው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ በዓሉ መከበሩ የጋራ እሴቶች በማጠናከር ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበትና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል። 

ብዝኃነት የሀገር ውበትና ሀብት በመሆኑ የተለያዩ ማንነቶችን በማክበር ሕዝቦችን በጋራ የሚያስተሳስሩ እሴቶችን ይበልጥ  ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ልዑልሰገድ አሰፋ በበኩላቸው፣ በዓሉ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ታሪካቸውንና ትውፊታቸውን እንዲያውቁ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል። 

ሕገ መንግስቱ የሕዝቦችን እኩልነት፣ የማንነት ክብር፣ የቋንቋና የባህል ብዝኃነት እንዲሁም በጋራ የመኖር መርሆዎችን ማረጋገጡን ነው ያመለከቱት።

እነዚህን መርሆዎች በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ በትብብር መሥራት ይገባል ነው ያሉት።


 

የሕዝቦች መብት መከበር፣ የሕግ የበላይነት መረጋገጥና የዜጎች በእኩልነት መሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት መሠረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ገዛኸኝ ክንዱ ናቸው። 

የ21ኛው ዓመት የብሔር ብሔረሰቦች በዓል መከበር የሕዝቦችን የጋራ እሴት በማጠናከር አንድነትን ለማጎልበት ሰፊ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም ገልጸዋል።

ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ በለጡ ሲሳይ በበኩላቸው፣ በዓሉ የተለያዩ ማንነቶችን ለማወቅና ለማክበር፣ የጋራ እሴቶችን ለማጠናከር እንዲሁም የመተማመንና የመተባበር ባህልን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል። 

ከበዓሉ አከባበር ባለፈ የጋራ ታሪክን በመረዳት የዜጎችን እኩልነት ለማረጋገጥ ያስችላል ሲሉም አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም