በፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከ11 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ህፃናት ተደራሽ ይሆናሉ- ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
በፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከ11 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ህፃናት ተደራሽ ይሆናሉ- ኢንስቲትዩቱ
ጨንቻ -ህዳር 12/2019 ዓ/ም /ኢዜአ/በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ11 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን ተደራሽ የሚያደርግ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ መስጠት ተጀመረ።
ፎቶ አለው
ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የዘመቻው ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶርዜ ላካና ማልዶ ቀበሌ ተካሂዷል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ መስፍን ወሰን፣ ኢትዮጵያ ፖሊዮን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት መጠነ ሰፊ ጥረት እያደረገች መሆኗንና በዚህም ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቧን ገልጸዋል።
ዘመቻው በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤት ለቤት እንደሚካሄድ ነው የጠቆሙት።
ከዚህ ቀደም ክትባቱን የወሰዱም ሆኑ ያልወሰዱ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከ11 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት እንደሚከተቡ ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ጤናማና አምራች ትውልድ ለመፍጠር ቢሮው በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፖሊዮ በሽታ በተበከለ ውሃ፣ ምግብና በእጅ አማካኝነት የሚተላለፍና በሀገር ልማት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ምንተስኖት መልካ (ዶ/ር) እንዳሉት ደግሞ፣ በክልሉ ብቻ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ክትባቱን ያገኛሉ።
መድኃኒት ያልተገኘለትን የፖሊዮ በሽታ በክትባት፣ በአሰሳና በቅኝት መቆጣጠር ስለሚቻል፣ የክልሉ ሕዝብ ለዘመቻው ስኬት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ፣ ዘመቻው በዞኑ በሚገኙ 14 ወረዳዎችና ሰባት ከተማ አስተዳደሮች እንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ ለወረርሽኝ ምላሽ ሥራዎች ውጤታማነት አስተዳደሩ ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የመጀመሪያው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከኅዳር 12 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ዙር ደግሞ ከአንድ ወር በኋላ እንደሚሰጥ ተመላክቷል።