ቀጥታ፡

ከድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል

ድሬዳዋ፤ ህዳር 12/2019 (ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና በበጀት አመቱ ሦስት ወራት ተመርተው ወደ ወጭ ሀገር ከተላኩ ምርቶች 3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለጸ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመተባበር " የላቀ ፋይናንስ አገልግሎት፤ ለነፃ ንግድ ቀጣናዎች ተወዳዳሪነት" በሚል ሀሳብ ያዘጋጀው ወርክሾፕ በድሬዳዋ ተካሂዷል።

የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አህመድ ረሺድ ለኢዜአ እንደገለፁት በቀጠናው የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በአምራች ኢንዱስትሪና በሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፎች በመሰማራት ውጤታማ ስራዎች እያከናወኑ ነው።

በነጻ ንግድ ቀጣናው በበጀት አመቱ ሦስት ወራት ወደ ውጭ ሀገራት ከተላኩ የኢንዱስትሪ ምርቶች 3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

ገቢው የተገኘው በቀጣናው ተመርተው ወደ ውጭ ሀገራት ከተላኩ የጥጥ ፈትልና ክር እንዲሁም የሲሚንቶ ምርቶች ማሸጊያ ከረጢቶች መሆኑን ጠቅሰዋል።

የነፃ ንግድ ቀጣናው የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባሻገር ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩንም አመልክተዋል።

የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች የአዳዲስ ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ባለቤት በመሆን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን በተግባር እያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል

በወርክ ሾፑ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራአስፈፃሚ ፅህፈት ቤት የፋይናንስ አማካሪ አቶ ፍፁም ግርማ የነፃ ንግድ ቀጠናዎች ዓለም አቀፍ የወጪና ገቢ ንግድ የሚካሄድባቸው በመሆኑ በፋይናንስና በሎጂስቲክ ተወዳዳሪነታቸውንና አሸናፊነታቸውን የማረጋገጥ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

ስራዎቹን በላቀ ቅንጅትና መናበብ በዘላቂነት በማስቀጠል በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር እስከ 2031 ድረስ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት የተወጠነውን ዕቅድ ለማሳካት እንደሚሰራ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም