በአፍሪካ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚከሰትን ሞት ለመግታት የጋራ ትብብርን ማጎልበት ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚከሰትን ሞት ለመግታት የጋራ ትብብርን ማጎልበት ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2019(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚከሰትን ሞት ለመግታት አስቀድሞ ምርመራ ማድረግ፣ ራሱን የቻለ የገንዘብ ምንጭ መመደብና የሁሉም አካላት የተቀናጀ ትብብር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው ዛሬ በአዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ዋና መሥሪያ ቤት መካሄድ በጀመረው የአፍሪካ ቀጠናዊ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጉባኤ ላይ ነው።
ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆየው ይህ ጉባኤ የአፍሪካ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ማኅበራት ጥምረት ከአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከልና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
ጉባኤው “ከቃል ኪዳን ወደ አፍሪካ-መር ተግባር፤ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ የጤና ደህንነትን፣ ራስን መቻልን እና አይበገሬነትን ማዳበር” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ ወቅት በጤና ሚኒስቴር የተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የአዕምሮ ጤና ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት አየለ፣ ኢትዮጵያ የአህጉሪቱን የጤና አጀንዳዎች በዓለም አቀፍ መድረክ በግንባር ቀደምትነት እያስተጋባች መሆኗን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኅብረትንና የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከልን መቀመጫ በመሆን እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ 76ኛ ጉባኤን በሊቀመንበርነት እየመራች መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፍ ከሚባሉት አንዱ የሆነውን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና ሥርዓት በመገንባት፣ ጤና ኬላዎችንና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በመጠቀም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ውስጥ በማካተት እየሠራች መሆኗንና በዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና ማግኘቷን አብራርተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር መሐመድ ያኩብ ጃናቢ፤ በአፍሪካ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት በየዓመቱ በርካታ አዋቂዎች ለሞት እንደሚዳረጉ ገልጸዋል።
በመሆኑም ምልክት እስኪታይ ሳይጠበቅ አስቀድሞ መመርመር፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል እና የሁሉንም አካላት ጠንካራ አጋርነት ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ራጂ ታጁዲን በበኩላቸው፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከ2030 በፊት ተላላፊ በሽታዎችን በመብለጥ በአፍሪካ ዋነኛ የሞት መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
በአፍሪካ ከሚከሰቱ ሦስት ሞቶች መካከል አንዱ በእነዚሁ በሽታዎች ምክንያት የሚከሰት መሆኑንም አብራርተዋል።
ለዘርፉ ራሱን የቻለ በጀት መመደብና አገልግሎቱን በማኅበረሰብ እና በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ሥርዓት ውስጥ ማካተት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዛንዚባር አብዮታዊ መንግሥት የጤና ሚኒስትር ናሶር አሕመድ ማዝሩይ፤ በዛንዚባር የማኅበረሰብ ጤና ሠራተኞችን በማሰልጠን ቤት ለቤት የቅድመ ምርመራ ሥራ መሠራቱንና ሴቶች የማኅጸን በርና የጡት ካንሰር ምርመራ እንዲያገኙ መደረጉን በተሞክሮ አንስተዋል።
አፍሪካውያን በሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮች ዘርፉን መደገፍና ሕሙማንን በውሳኔ ሰጪነት ማሳተፍ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስብሰባዎቻችንን 10 በመቶ በውይይት፣ 90 በመቶ በተግባር እናድርግ የሚለው መርህ የሚደነቅ መሆኑንና አፍሪካውያን ቃል ኪዳኖቻቸውን ወደ ተጨባጭ ሥራ መለወጥ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።