በአማራ ክልል የደረሰ የስንዴ ሰብል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ እየተሰበሰበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የደረሰ የስንዴ ሰብል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ እየተሰበሰበ ነው
ባህር ዳር፤ ህዳር 12/2019 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የደረሰ የስንዴ ሰብል እየጣለ ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በኮምባይነር በመታገዝ እየተሰበሰበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው የድኅረ ምርት ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ምትኩ መላኩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በ2018/19 የመኸር ወቅት በክልሉ ከ1 ሚሊዮን 80 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ለምቷል።
እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም በ86 ሺህ 300 ሄክታር ላይ የደረሰ ስንዴ የተሰበሰበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 22 ሺህ 400 ሄክታሩ በኮምባይነር ታግዞ መሰብሰቡን ነው የጠቀሱት።
ከዚህም ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን አመልክተዋል።
ሰብሉ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ከ90 የሚበልጡ የሰብል ማጨጃና መውቂያ ኮምባይነሮች በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሰው ጉልበትና በኮምባይነር ታግዞ የደረሰን የስንዴ ሰብል ከብክነት በጸዳ መልኩ በመሰብሰብ የተሻለ ምርት ይገኛል ተብሎ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።
የሚሰበሰበው የስንዴ ምርት ከራስ ፍጆታ ባለፈ ዱቄትን ጨምሮ ለፓስታና መኮሮኒ ፋብሪካዎች በግብዓትነት እንደሚቀርብም ጠቁመዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን የባሶ ሊበን ወረዳ አርሶ አደር ሰውመሆን ባዬ እንዳሉት፤ ሁለት ሄክታር በሚጠጋ መሬት ያለሙትን የስንዴ ሰብል በኮምባይነር መሰብሰብ ጀምረዋል።
እስካሁን በኮምባይነር ከሰበሰቡት አንድ ሄክታር የሚጠጋ መሬት 30 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደቻሉ ጠቅሰው ቀሪውን የመሰብሰብ ሥራ በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየሠሩ እንደሆነም አመልክተዋል።
በዘንድሮው የመኸር ወቅት በክልሉ አጠቃላይ በተለያዩ ሰብሎች ከለማው ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እስካሁን በ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰብ መቻሉን የቢሮው መረጃ ያመለክታል።