በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ከ6 ሺህ 400 በላይ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲገቡ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ከ6 ሺህ 400 በላይ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲገቡ ተደርጓል
ህዳር 12/2019 ጭሮ(ኢዜአ) በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ባለፉት አራት ወራት ከ6 ሺህ 400 በላይ ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት መግባታቸውን የዞኑ ንግድ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የፅህፈት ቤቱ ሀላፊ ተወካይ አቶ ጀማል ቃሲም ለኢዜአ እንደገለፁት ነጋዴዎቹ ወደ ህጋዊ ስርዓቱ የገቡት በዞኑ በ36 ወረዳዎች እና ጭሮ፣ ሂርና፣ ገለምሶ እና ደደርን ጨምሮ በሰባት ከተሞች በተካሄደ የንግድ ድርጅቶች ቁጥጥርና ምልከታ ነው።
በወራቶቹ በንግድ ስራ ላይ በነበሩ 27 ሺህ 800 በላይ ድርጅቶች ላይ ጭምር የቁጥጥርና ምልከታ ስራ መካሄዱን ጠቁመዋል።
በንግድ ቁጥጥና ምልከታ ሂደቱ ከ6ሺህ 400 በላይ ነጋዴዎች ከህጋዊ አሰራር ውጪ በመሆናቸው ወደ ህጋዊ ስርዓቱ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል ።
በቁጥጥሩ ተለይተው ወደ ህጋዊ ስርዓቱ እንዲገቡ የተደረጉት ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድ፣ በመንገድ ዳርቻ የንግድ ሥራ ማከናወን፣ በሌሎች ሰዎች ፈቃድ ተጠቅሞ መነገድ እና በመሳሰሉት ከሕግ አግባብ ውጭ የተሰማሩ እንደሆኑ ገልፀዋል።
ከዚሁ በተጓዳኝ የንግድ ፈቃድና የዋጋ ዝርዝርን በሚታይ ቦታ ሳይለጥፉ የተንቀሳቀሱና ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎችም በቁጥጥሩ ተለይተው አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ሕጋዊ የንግድ ስርዓቱን ለማጠናከር እንዲሁም ሸማቹን ተገቢ ካልሀነ የዋጋ ጭማሪ ለመከላከል የተለያዩ አካላትን ያሳተፈ የንግድ አሰራር ቁጥጥር ግብረ ሀይል ተቋቁሞ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።