በማህበር በመደራጀት በሌማት ትሩፋት የንብ ማነብ ስራ በመሰማራት የተሻለ ገቢ ማግኘት ችለናል -አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በማህበር በመደራጀት በሌማት ትሩፋት የንብ ማነብ ስራ በመሰማራት የተሻለ ገቢ ማግኘት ችለናል -አርሶ አደሮች
ቦንጋ ፣ ህዳር 12 /2019 (ኢዜአ)፦ በካፋ ዞን ሺሾ-እንዴ ወረዳ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሩ የንብ ማነብ ሥራ ላይ በመሰማራት የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ በበኩሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከ85 ሺህ ቶን በላይ ማር ለማምረት እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል።
በካፋ ዞን ሺሾ-እንዴ ወረዳ ዋረታ ቀበሌ የሚገኘው "ቤሞ ሹኖና" የተሰኘው ሞዴል የንብ መንደር በዓመት ከ40 ነጥብ 5 ቶን በላይ የማር ምርት ለገበያ ያቀርባል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት የሞዴል መንደሩ አባላት መካከል አርሶ አደር ሰይድ ሁሴን በንብ ማነብ ሥራ በመሰማራት የተሻለ ጥቅም እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይ 150 ቀፎ ያላቸው መሆኑን ገልጸው ከአንድ ቀፎ እስከ 50 ኪሎ ግራም ምርት በማምረት እስከ 500 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ ነው የተናገሩት።
በ22 ቀፎች በሚያካሂዱት የንብ ማነብ ሥራ ውጤታማ እንደሆኑ የሚናገሩት ሌላው አርሶ አደር አደም መሐመድ በዚህም በዓመት እስከ 40 ሺህ ብር ድረስ ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
በቀጣይ የቀፎ ቁጥራቸውን በሰፊው በመጨመር ከዘርፉ የሚያገኙትን ጥቅም ለማሳደግ ዕቅድ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በቦንጋ ከተማ በማር ማምረትና ማቀነባበር ሥራ ላይ የተሰማራው አፒኔክ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ተስፋዬ ማኅበሩ በራሱ የሚያመርተውንና ከአርሶ አደሮች የሚሰበስበውን ማር በማቀነባበር ሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
ማኅበሩ ባሉት ዘመናዊ የማቀነባበሪያ ማሽኖች ምርቱን በማቀነባበር ለገበያ እንደሚያቀርብ አንስተዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእንስሳትና ዓሣ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ በቀለ በበኩላቸው፤ በክልሉ ባለፉት አራት ዓመታት 980 የማር መንደሮች መደራጀታቸውን ተናግረዋል።
የሌማት ትሩፋት ከመጀመሩ በፊት የክልሉ ዓመታዊ የማር ምርት 56 ሺህ ቶን እንደነበር አስታውሰው ከሌማት ትሩፋት መጀመር በኋላ 80 ሺህ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
በተያዘው ዓመት የተደራጁ ማኅበራትን ሞዴል አድርጎ ምርታማነትን ይበልጥ በማሳደግ የምርት መጠኑን 85 ሺህ ቶን ለማድረስ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።