የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትንና ዕድገትን የሚያረጋግጥ መሰረታዊ ጉዳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትንና ዕድገትን የሚያረጋግጥ መሰረታዊ ጉዳይ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2019(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በሕግ፣ በኢኮኖሚ የዕድገት ፍላጎትና በመልክዓ ምድራዊ ቅርበት ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የቀድሞ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሞቱማ መቃሳ ገለጹ።
የባሕር በር ከንግድና ከምጣኔ ሀብት ፋይዳ ባሻገር ዓለም አቀፋዊ ትስስርን፣ የጋራ ተጠቃሚነትን፣ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችንና ሌሎች ጠቀሜታዎችን ማረጋገጥ የሚቻልበት ወሳኝ መሰረተ ልማት መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከታሪካዊ ቁጭት ወደ ብሔራዊ ድል የሚያሸጋግር መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ፣ ለምላሹ የሁሉንም ጥረት የሚጠይቅ ነው።
ኢትዮጵያ ለዘመናት ይዞታዋ በነበረው የባሕር በር ጥቅሟንና ክብሯን አስጠብቃ የኖረች ብትሆንም፣ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በውል ባልታወቀ ምክንያት ከባሕር እንድትርቅ ተደርጓል።
በኢኮኖሚ ዘርፍ ፈጣን ዕድገትና በአፍሪካ ሁለተኛውን የሕዝብ ቁጥር የያዘችው ኢትዮጵያ ከባሕር በቅርብ ርቀት ላይ ተገኝታ የባሕር በር አልባ ሆና መቀጠሏ የማይቻልና የህልውና ጉዳይ ነው።
ይህ ጉዳይ ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲነሳ የኖረ፣ ምላሽ ያላገኘና በሀገራዊ ቁጭትነት የቆየ ታሪካዊ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር መውጫዋን ማጣቷ በሀገራችን የታሪክ፣ የፖለቲካና የብሔራዊ ጥቅም ጉዞ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳረፈ ክስተት መሆኑም ይነሳል።
በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ የባሕር በር ባለቤትነት ታሪካዊ ጥያቄዋ ምላሽ እንዲያገኝና እንዲረጋገጥ እየሰራች ትገኛለች።
በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳባቸውን ያጋሩት የቀድሞ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገርና ኢኮኖሚዋም በማደግ ላይ ስለሆነ ይህ ዕድገት ታፍኖ ሊቀጥል እንደማይችል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አሁን በቀይ ባሕር በኩል ባላት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በታሪክም ሆነ በሕግ የባሕር በር ባለቤትነቷን የማረጋገጥ መብት እንዳላት ገልጸዋል።
በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ረገድ ከቀይ ባሕር ከ40 እስከ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በጣም ቅርብ ሆና መገኘቷ ጉዳዩን ተግባራዊ እንደሚያደርገው አመልክተዋል።
በታሪክ የኢትዮጵያ የነበረ የባሕር በር ባለቤትነትም መመለስ ያለበት የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሕጋዊነት በኩልም በዓለም አቀፍ ሕግ ኢትዮጵያ ወደቡን የመጠቀም መብቷ የተጠበቀ በመሆኑ፣ አሁን የተጀመረው ጥረት እጅግ አስፈላጊና ትክክል መሆኑን አስረድተዋል።
የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ከኢትዮጵያ ባሻገር ለቀጣናው ሀገራትም ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት የቀድሞ ሚኒስትር፣ ለቀጣናው ደህንነት መረጋገጥም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የቀጣናው ሀገራት የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለጋራ ተጠቃሚነት ሊደግፉ እንደሚገባ ገልጸዋል።