በድሬደዋ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ ገቡ
ድሬደዋ፤ ህዳር 12/2018(ኢዜአ)፦ በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ጥናት፣ መረጃ ዝግጅትና ፕሮሞሽን ቡድን አስተባባሪ አቶ አበራ መንግሥቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በድሬዳዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚመጡ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
ለዚህም እየተፈጠረ ያለው ምቹ የሥራ ከባቢና የሚደረገው የኢንቨስትመንት ማበረታቻና ድጋፍ ትልቁን ስፍራ ይይዛል ነው ያሉት።
በተለይም ለአዳዲስ ባለሀብቶች መሠረተ ልማትን በማሟላት፣ መስሪያ ቦታና መሬት በማዘጋጀት፣ ከቀረጥ ነፃ እድልን እንዲጠቀሙ በማድረግ፣ የታክስ እፎይታ በመፍቀድና ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
በዋናነት ባለፉት ሁለት ዓመታት በድሬዳዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለሥራና ለኑሮ ምቹ በማድረጉ በአካባቢው መዋእለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የሚመጡ ባለሃብቶች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን አመልክተዋል።
ለወደብ ያላት ቅርበትና በሁሉም መሠረተ ልማቶች የተሳሰረች መሆኗ ለኢንቨስትመንት ተመራጭነቷን የሚያጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
እነዚህን የተፈጠሩ ምቹና የተደላደሉ ሁኔታዎች በመጠቀም በመጀመሪያሩ ሩብ የበጀት ዓመት ብቻ ከ14 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 135 ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ፈቃድ ወስደው በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎትና በግብርና ዘርፎች የተሰማሩት ባለሀብቶች እስከ ሦስት ዓመት ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ ማምረት ሲሰማሩ ለ3 ሺህ ሰዎች ቋሚ እና ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር በግንባታ ላይ ለሚገኙ ባለሀብቶች በሚያደርገው የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል በሩብ ዓመቱ እስከ ስድስት ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ አድርጓል ነው ያሉት።