የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2019 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስድሰተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ በስድስት ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
የወቅቱ ሻምፒዮን ሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ሲዳማ ቡና በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ተሳትፎው ምክንያት ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀሩታል።
አዳማ ከተማ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አላሸነፈም።
ጨዋታው ሲዳማ ቡና የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት፣ አዳማ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
በሌላኛው መርሐ ግብር ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 10 ሰዓት በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ባለሜዳው ባህር ዳር ከተማ በሰባት ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በተመሳሳይ ሰባት ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በአምስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ባህር ዳር ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር ሁለት አቻ ሲለያይ ኢትዮጵያ መድን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3 ለ 1 ረትቷል።
ሁለቱ ቡድኖች በተመሳሳይ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አላቸው።
ሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻን ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያገናኛል።
ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አራት ነጥብ በማግኘት 14ተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ በተመሳሳይ ከአምስት ጨዋታዎች ስምንት ነጥብ በመሰብሰብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቡናማዎቹ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ድል አልቀናቸውም።
ወላይታ ድቻ ያለፉትን ሁለት የሊግ ጨዋታዎች በድል ተወጥቷል።
ጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ፣ ወላይታ ድቻ በድል ጉዞ ለመቀጠል የሚያደርጉት ነው።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ሸገር ከተማ ከሀዋሳ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ሸገር ከተማ በአምስት ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያለው ሀዋሳ ከተማ በተመሳሳይ አምስት ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሸገር ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
በአምስተኛ ሳምንት ጋሞ ጨንቻን 2 ለ 1 በማሸነፍ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ያገኘው ሀዋሳ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል።