ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ቃል ኪዳኖች ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዲቀየሩ በቁርጠኝነት ትሰራለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ቃል ኪዳኖች ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዲቀየሩ በቁርጠኝነት ትሰራለች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በኮፕ 32 የአየር ንብረት ቃል ኪዳኖች ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዲቀየሩ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ከህንድ የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ቡፔንደር ያዳቭ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱም የፓሪስ ስምምነትን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መተግበር አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል።
በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች በአየር ንብረት ፋይናንስ፣ በዘላቂ ልማት፣ እንዲሁም ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ወዳለውና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ሀገራት በራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ የሚቀርጿቸው አካሄዶች ስላላቸው ወሳኝ ፋይዳ በጥልቀት መክረዋል።
ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ የምታስተናግደውን ኮፕ 32 አስመልክቶ ባነሱት ሀሳብ ኢትዮጵያ ሰፊና ሁሉን አቀፍ ምክክር ለማድረግ እንዲሁም ሀገራት ከአየር ንብረት ቃል ኪዳኖች ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዲሸጋገሩ የሚያስችሉ ስራዎችን ለማራመድ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ይህም የሁለተኛውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት አፈጻጸም ግምገማ (Global Stocktake) ቴክኒካል ስራዎች ማሳደግን እና ሀገራት ብሔራዊ ከአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም ዕቅዶቻቸውን እንዲተገብሩ የሚሰጠውን ድጋፍ ማጠናከርን ያካትታል።
ህንድ ለደቡቡ ዓለም ክፍል ያላትን ጠንካራ ድምጽ በመገንዘብ፣ ፍትሃዊነትን የሚያጎለብቱና ሀገራት የልማትም ሆነ የአየር ንብረት ቅድሚያዎቻቸውን በፋይናንስ መደገፍ የሚችሉበትን ውጤት ለማምጣት በቀጣናዎች መካከል ትብብርን በመገንባት ረገድ የምትጫወተውን የመሪነት ሚና ኢትዮጵያ በአዎንታ እንደምትመለከተው ተመራጭ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
#COP31 #COP32 #ClimateAction