ቀጥታ፡

የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋዜጠኛ መግደላዊት ነጋ የኢጋድ ሚዲያ ሽልማት አሸናፊ ሆነች

አዲስ አበባ፤ሕዳር 11/2019 (ኢዜአ)፡- የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ (ፒኦኤ )ጋዜጠኛ መግደላዊት ነጋ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በአየር ንብረት ለውጥ እና በግጭት ምክንያት በሚከሰት መፈናቀል ዘርፍ (Climate and Conflict-Induced Displacement) ላይ በሰራቸው ፕሮግራም የ2026 የሚዲያ ሽልማት አሸናፊ ሆናለች።

ሽልማቱን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እጅ ተረክባለች።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የ2026 የሚዲያ ሽልማት በዩጋንዳ ካምፓላ እየተካሄደ ይገኛል።

“ የሰዎች ዝውውር ለቀጣናዊ ትስስር፡ ነጻ እንቅስቃሴ፣ ምቹ የሥራ ዕድል፣ ጥበቃ እና የጋራ ብልጽግና” የዘንድሮው ሽልማት መሪ ሀሳብ ነው።

በመድረኩ የኢጋድ ዋና ፀሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የዩጋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቢናህ ናባንጃ፣ ተሸላሚ ጋዜጠኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩም የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋዜጠኛ መግደላዊት ነጋ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የ2026 የሚዲያ ሽልማት በአየር ንብረት ለውጥ እና በግጭት ምክንያት በሚከሰት መፈናቀል ዘርፍ ስር በሰራቸው ፕሮግራም ሽልማቷን ወስዳለች።

ፕሮግራሙ “How Opportunity Changed Everything | The Story of Faduma Abukar” የሚል ርዕስ ያለው ነው።

ይህ ፕሮግራም ሕይወቷ ግጭት፣መፈናቀል እና ጽናትያልበገረውንና ይልቁንም ማንነቷን የገነባውን የፋዱማ አቡከርን አስደናቂ ታሪክ ላይ ያተኮረ ነው።

በሶማሊያ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ሀገሯን ጥላ ለመሰደድ የተገደደችው ፋዱማ፣በየመን ከለላ ብትፈልግም እዚያም በተከሰተ ሌላ ግጭት በድጋሚ ተፈናቅላ በመጨረሻ በኢትዮጵያ መጠለያ አገኘች።

ይሁን እንጂ ይህ በሕይወት የመትረፍ ታሪክ ብቻ አይደለም።

ጥበቃ ከምቹ ዕድል ጋር ሲጣመር ምን ሊፈጠር እንደሚችል የሚያሳይ ታሪክ ነው።ፋዱማ በኪነ-ጥበብ፣ በአካታችነት እና ትርጉም ያለው ሥራ በማግኘት የራሷን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የቀየረች ሲሆን፣ ሌሎችም ተመሳሳይ ለውጥ እንዲያመጡ መርዳት ጀምራለች።

ከአዚዝ ሃዚዚ ጋር በመሆን በስደተኞች የተደራጀ እና በስደተኞች የተገነባውን ''ሻማ'' (Shama) የተሰኘ ተቋም ያቋቋመች ሲሆን፣ ይህም ሰዎች አስተዋጽኦ የማድረግ ዕድል ሲሰጣቸው በዙሪያቸው ያሉትን ማኅበረሰቦች እንደሚያግዙና እንደሚቀይሩ በተግባር ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም