በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ጋዜጠኝነት ለቀጣናው ሰላም፣ ትስስርና የጋራ ብልጽግና ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ጋዜጠኝነት ለቀጣናው ሰላም፣ ትስስርና የጋራ ብልጽግና ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፦ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ጋዜጠኝነት ለቀጣናው ሰላም፣ ትስስርና የጋራ ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።
እ.ኤ.አ. የ2026 አራተኛው የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት ሥነ-ሥርዓት በኡጋንዳ ካምፓላ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ጥራት ያለውና በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ጋዜጠኝነት ለቀጣናው ሰላም፣ ትስስርና የጋራ ብልጽግና ወሳኝ ነው።
በፍጥነት በሚለዋወጥና የተለያዩ ትርክቶች በሚንሸራሸሩበት ወቅት ሐቀኛ ዘገባ ቅንጦት ሳይሆን ለሕዝብ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል።
በደንብ የተተረከ ታሪክ የተዛቡ ቅድመ ግምቶችን የማፍረስ፣ የተሳሳቱ መረጃዎችን የመግታትና ቀጣናው ለተግባር እንዲነሳሳ የማድረግ አቅም እንዳለውም ገልጸዋል።
የሰዎችን እንቅስቃሴ እንደ ቀጣይ ቀውስ ምክንያት ብቻ አድርጎ ከማየት ይልቅ የቀጣናው ጥንካሬና የትስስር ሞተር ሊሆን እንደሚችል መመልከት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ኢጋድ 40ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን እያከበረ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዋና ፀሐፊው ድርቅንና የምግብ ዋስትና እጦትን በጋራ ለመጋፈጥ የተጀመረው ትብብር በሰላምና ደኅንነት፣ በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋምና በኢኮኖሚ ትስስር ላይ የተመሠረተ ሁሉን አቀፍ ማዕቀፍ ወደ መሆን ማደጉን ተናግረዋል።
የ40 ዓመታት የጋራ ታሪክም ቀጣናዊ ትብብር የህልውና ግዴታ መሆኑን የሚያረጋግጥ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የዘንድሮው የሽልማት አሸናፊዎች የተሳሳቱ አመለካከቶች እንዲስተካከሉ በመሥራት የሰዎችን እንቅስቃሴ በጋራ ሰብዓዊነት መነጽር እንዲታይ በማድረጋቸው ምስጋና አቅርበዋል።
ቀጣናውን በሰላም፣ በጥልቅ ትስስርና በጋራ ብልጽግና ለማስተሳሰር ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።