ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ማዕከል ለመሆን የጀመረችውን ተግባራት አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ማዕከል ለመሆን የጀመረችውን ተግባራት አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) አስታወቁ።

ኢንስቲትዩቱ በሥሩ በተቋቋመው ''ኤይ አይ ዩኒፖድ'' (AI UniPod) ማዕከል የሰለጠኑና የፈጠራ ሐሳብ ያላቸውን አፍሪካውያን ስታርትአፖች አስመርቋል።በማዕከሉ ከ12 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ስታርትአፖች የፈጠራ ሐሳባቸውን ወደ ተግባር ማውረድ የሚያስችላቸውን የቴክኒክና የቢዝነስ አተገባበር ሥልጠናዎችን ወስደዋል።


የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሰልጣኞች የፈጠራ ሐሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችላቸውን ጥልቅ ሥልጠና አግኝተዋል።

ከሥልጠናው ጎን ለጎን እርስ በእርስ የፈጠሩት ጥልቅ ግንኙነት ለአፍሪካ መጻኢ ዕድገት ትልቅ ሀብት መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ አህጉሪቱን ለመለወጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

አፍሪካ በራሷ አቅም የሚመራ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የመገንባት ሕልሟ እውን እንደሚሆን ሙሉ እምነት እንዳላቸውም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ ከዜጎቿ ባሻገር በአፍሪካ ያሉ ታዳጊዎችንና ወጣቶችን በማሰልጠን ዝግጁ የማድረግ ሥራዎችን በስፋት እያከናወነች መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሀገሪቱ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ የአፍሪካ ማዕከል ለመሆን የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።


የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (ዩኤንዲፒ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የዓድዋን ድል በማብሰር ለአፍሪካውያን ነጻነት መሠረት የሚሆን አሻራ ማኖሯን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ አፍሪካ በሰው ሠራሽ አስተውሎት መሪ እንድትሆን በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን የሚያረጋግጡ ውጤቶች እየታዩ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ የተጀመረው የመደመር የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታና ሌሎች ልማቶች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ተመራቂ አፍሪካውያን ወጣቶች የአህጉሪቱ የወደፊት ተስፋዎች መሆናቸውን ያነሱት ተወካዩ፤ ''ያላችሁን የፈጠራ ሐሳብ ወደ ተግባር በማውረድ የድርሻችሁን ልትወጡ ይገባል''ሲሉ አሳስበዋል።


የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅትም ዓላማቸው ግቡን እንዲመታ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም