ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች በሀገራዊ ውሳኔዎች ላይ ተጨባጭ ተጽዕኖ እንዲያሳርፉ አድርጓል

አዳማ፤ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች በሀገራዊ ውሳኔዎች ላይ ተጨባጭ ተጽዕኖ እንዲያሳርፉ ዕድል መፍጠሩን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አየለች እሸቴ አስታወቁ።



በሀገራዊ ምክክር ሂደት የሴቶች ተሳትፎ፣ የተገኙ ተሞክሮዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ለሦስት ቀናት የሚመክር ዐውደ ጥናት በአዳማ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔና የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አየለች እሸቴ እንዳሉት፤ ''ሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች በንቃት የምንሳተፍበትን፣ ድምጻችን የሚሰማበትንና በሀገራዊ ውሳኔዎች ላይ ተጨባጭ ተጽዕኖ የምናሳርፍበትን ሰፊ ዕድል ከፍቶልናል'' ብለዋል።

ፌዴሬሽኑ በምክክሩ ሂደት ሴቶች ጥያቄዎቻቸውን በተደራጀ መልኩ እንዲያቀርቡ መሥራቱን የገለጹት ምክትል አፈ ጉባዔዋ፤ የተፈጠረውን መነቃቃት ወደ ዘላቂ ሀገራዊ ጥቅም ለመለወጥ የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች የተቀናጀ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት (UN Women) የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ነጋ ገርባባ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ከፌዴሬሽኑና ከአጋሮች ጋር በመተባበር ሴቶች በምክክሩ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።


የፌዴራል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በምክክሩ ሂደት በአወያይነት፣ በታዛቢነትና በአማካሪነት የላቀ ሚና መጫወታቸውን አመልክተዋል።


ዐውደ ጥናቱን የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ከተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም