ቀጥታ፡

በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች የመደመር መንግሥት ቁርጠኝነት ሕያው ምስክሮች ናቸው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፦ በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች የመደመር መንግሥት ለትውልድ ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ሕያው ምስክሮች ናቸው።

የመደመር ፍልስፍና በመሰባሰብ፣ በመቀናጀት፣ አቅምን በማዋሃድና በትብብር በመሥራት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሳቤ ነው። አካታችነት፣ ሚዛናዊነት፣ ቀጣይነት ያለው መሻሻልና ትብብር የዚህ ፍልስፍና ወሳኝ አዕማድና የስኬት ቁልፎች ናቸው።

በመደመር እሳቤ የሰው ልጅ ክብር፣ የሥራ ባህል አብዮትና ማኅበራዊ መስተጋብር ዋነኛ ማጠንጠኛዎቹ ሲሆኑ፤ የመደመር መንግሥትም ትምህርትን ለሰው ሀብት ልማት፣ ለሀገር ግንባታና ለዳበረ አስተሳሰብ ለውጥ ዋነኛ መሣሪያ አድርጎ የሚወስድ ተራማጅና ዘመኑን የዋጀ አተያይ አለው።

በዚህም መሠረት መንግሥት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ለተሻለ ትውልድና ለበለጸገች ሀገር ጽኑ መሠረት መሆኑን በመገንዘብ፣ በዚሁ እሳቤ የተቃኘ የትምህርት ፖሊሲ አውጥቶ ተግባራዊ አድርጓል።

የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ቅንጦት ሳይሆን ለሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች እኩል መዳረስ ያለበት ሀገራዊ ኢንቨስትመንት በማድረግም በመላ ሀገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችን አስገንብቷል።

በዚህ ቁርጠኝነት ወደ 35 ሺህ በሚጠጉ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት የትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲገኙ ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ''ትምህርት ለትውልድ''በሚል መሪ ሐሳብ ባስጀመሩት ሀገራዊ ንቅናቄም መንግሥት ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል በማስተባበር ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል።

በዚህም ከ17 ሺህ በላይ አዳዲስ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲገነቡ፣ 40 ሺህ የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ዕድሳት ተደርጎላቸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር በመንግሥት አስተባባሪነትና በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች የመደመር መንግሥት የልማት አቅጣጫ ውጤታማነት ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።

በከተማ አስተዳደሩ ፉሪ ክፍለ ከተማ የጨፌ ኦዳ ቡኡራ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት የወላጅ ኮሚቴ አባል አቶ አብደላ ክፍሉ እንደገለጹት፤ መንግሥት በአካባቢው ትምህርት ቤት አለመኖሩን በመገንዘብ ኅብረተሰቡን አስተባብሮ ትምህርት ቤቱ እንዲገነባ አድርጓል።

የዜጎችን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ትምህርት ቤቱ በአጭር ወራት ውስጥ መገንባቱን የጠቆሙት አቶ አብደላ፣ ከዚህ ቀደም ብዙ ወላጆች በትራንስፖርትና በኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያት ልጆቻቸውን ቤት ለማዋል ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል።

የዶሎሎ ቡኡራ ቦሩ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት መምህር መገርሳ ጋሹ በበኩላቸው፤ በአካባቢው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ማኅበረሰቡ ለከፍተኛ ችግር ተዳርጎ እንደነበር ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ትብብር ከተገነባ በኋላ ግን የተማሪዎች ምገባን ያካተተ የተሟላ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን አብራርተዋል።

በዚሁ ትምህርት ቤት ልጃቸውን የሚያስተምሩትና በተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወይዘሮ መሰረት ጋዲሳ፤ ቀደም ሲል ልጃቸውን በከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ሩቅ ቦታ ወስደው ሲያስተምሩ ለከፋ እንግልት ይዳረጉ እንደነበር ተናግረዋል።

ከአራት ዓመት በላይ ሥራ አጥተው ቤት ይውሉ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ መሰረት፤ ''መንግሥት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ'' እንዲሉ ልጆቼ ምገባ በሚያገኙበት ትምህርት ቤት ለእኔም የሥራ ዕድል ፈጥሮልኛል» ብለዋል።

የጨፌ ኦዳ ቡኡራ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት መምህርትና ልጃቸውን በዚሁ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት መምህርት ዝናሽ ተሾመ በበኩላቸው፤ እናት ሆነው ሩቅ ቦታ እየተጓዙ ማስተማርና ሕፃናትን ከፉሪ እስከ ጀሞና ጋርመንት ድረስ ማመላለስ እጅግ ፈታኝ እንደነበር ገልጸዋል።

ይህ ትምህርት ቤት መገንባቱ ለልጃቸው በቅርበት የመማር፣ ለእርሳቸው ደግሞ በአቅራቢያቸው የመሥራት ዕድል በመፍጠር ችግራቸውን እንደቀረፈላቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም