ቀጥታ፡

የአዕምሮና የነርቭ ሕክምና አገልግሎትን ማሳደግ የሚያስችል የኒውሮሎጂ መመሪያ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የአዕምሮና የነርቭ ሕክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ማሳደግ የሚያስችል የኒውሮሎጂ መመሪያ ይፋ ሆኗል።

በኢትዮጵያ የአዕምሮና የነርቭ ሕክምና አማራጮችን በማስፋት የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን የሚያረጋግጥ አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኒውሮሎጂ ማኅበር 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በአዲስ አበባ ያከበረ ሲሆን፤ በመርሐ-ግብሩ ላይ ከጤና ሚኒስቴርና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኒውሮሎጂ መመሪያ ይፋ ሆኗል።

በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የአዕምሮ ጤና ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት አየለ በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ልማት ውጤታማ ናቸው ብለዋል።

በአዕምሮና የነርቭ በሽታ የሕክምና አገልግሎትም የጉዳዩን ውስብስብነት ታሳቢ በማድረግ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ በሚባሉ የጤና ተቋማት ጭምር አገልግሎቱን በማስፋት ውጤታማ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኒውሮሎጂ መመሪያውም ሙያተኞች በሁሉም ጤና ተቋማት የመጀመሪያ ደረጃ የአዕምሮና የነርቭ ሕክምና እርዳታን በቀላሉ እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

ይህም በሽታው የተባባሰ ደረጃ ላይ ሳይደርስ በአጭሩ ማከም እንዲቻል የሚያግዝና የሕክምና ተቋማት በዘርፉ ያላቸውን አቅም ከፍ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

የባለሙያዎች አቅም ግንባታ፣ የመመርመሪያ መሣሪያና የመድኃኒት አቅርቦትን በአንድ ቦታ በማሟላት የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየተገነባ መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ኒውሮሎጂ ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰብለወንጌል አስማረ በበኩላቸው፤ መንግሥት ለአዕምሮና ነርቭ ሕክምና የሰጠው ትኩረት የአገልግሎት ተደራሽነቱን እያሳደገ ነው ብለዋል።

የኒውሮሎጂ መመሪያም ከመጀመሪያ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ፈጣንና ቀልጣፋ የአዕምሮና ነርቭ ሕክምና እንዲሰጡ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።

የዘርፉ የሕክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው መመሪያው ፈጣን የሕክምና እርዳታን ለመስጠትና በሕክምናው ዙሪያ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት የሚረዳ ነው ብለዋል።

የሕፃናት የነርቭ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር በኃይሉ ይቤ እንዳሉት፤ መመሪያው በአጋጣሚ የሚከሰቱ የስትሮክና መሰል የአካል መስነፍ ችግሮች ፈጣን ሕክምና እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

መመሪያው የኒውሮሎጂ ሕክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የነርቭ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሃና ደምሴ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም