ቀጥታ፡

ጀፎረ -የጉራጌ የውበት፣ የአብሮነትና የባህል መገለጫ

በእንዳልካቸው ደሳለኝ

የጉራጌን ማህበረሰብ ስናስብ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ በህሊናችን ቀድሞ ትውስ የሚለን ክትፏቸው አሊያም የጉራጊኛ ጭፈራቸው ሊሆን ይችላል። ክትፎውም ሆነ ጭፈራቸው በብዙዎች ዘንድ የሚወደድና የሚታወቅ ነው። ሌላው መታወቂያቸው ደግሞ የመንደር አመሰራረታቸውና የሣር ቤት አሰራራቸው ነው።

በተለይ ማራኪ የመንደር ገጽታ እንዲኖራቸው ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ከሚታወቁበት የምሕንድስና ጥበባቸው አንዱ "ጀፎረ" የተሰኘው መንደራቸው ነው። የጉራጌ መንደር አመሰራረት ያለ ጀፎረ አይታሰብም፡፡ ጀፎረ አረንጓዴ ሣር የለበሰ እና በሁለት ትይዩ መንደሮች መካከል የሚገኝ ሰፊ ባህላዊ አውራ መንገድ ነው፡፡ ለአካባቢው ነዋሪዎች መተላልፊያ መንገድ ሆኖ ያገለግላል፡፡ 

በጉራጌኛ "ጀፎረ" ማለት አውራ መንገድ እንደ ማለት ነው፡፡ ጀፎረ ከመሠረታዊ ጠቀሜታው ባለፈ ለተለያዩ ማህበራዊ ሁነቶች መከወኛም ሆኖ ያገለግላል። ለጉራጌ መንደሮች ውበት መላበስም እያደረገ ያለው አስተዋጾ የጎላ ነው፡፡

በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ "ጀፎረ" ከምቹ የመኖሪያ አካባቢነት በላይ የህብረተሰቡን ባህል፣ ወግ፣ የሞራል ልዕልና እና ማህበራዊ መስተጋብር በአንድ ላይ አጣምሮ ይዞ ከዘመን ዘመን ሲሸጋገር የመጣ ነው።

የጀፎረ መንደር ለጉራጌ ማህበረሰብ ውበት ብቻ ሳይሆን የሰላም፣ የፍቅር እና የአብሮነት ማህተም ጭምር ነው።  አንድነት እና ወጥነትን የሚያንጸባርቅ የማህበራዊ ትስስር ማዕከልም ነው።

የማህበረሰቡ አባላት በዕለት ተዕለት ኑሯቸው፣ በባህላዊ እሴቶቻቸው እና በሚያሳዩት የትብብር መንፈስ አንድነታቸውን የሚያንፀበረቁበት የወል ስፍራም ነው። መንደሩ የወል እሴቶችን በጋራ ጠብቆ የማቆየት ልምድ ማሳያም ተደርጎ ይወሰዳል።

በባህላዊ መንደሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሁም የህዝብ አስተዳደርና መሰል ጉዳዮች በጋራ ይመከርበታል፤ ይወሰንበታል። በተለይ እንደ ሠርግና ለቅሶ ያሉ ማህበራዊ ጉዳዮች የሚከወኑበት በመሆኑ የሕብረተሰቡ የአብሮነት እሴት ማጠናከሪያም ሆኖ ያገለግላል 

ድንገት እግር ጥሎት አሊያም አካባቢውን ለመጎበኘት ያቀና ሰው በጀፎረ ባህላዊ የመንደር አመሰራረት ቀልቡ ይሳባል። አንዳች የግርምት ስሜትም ያድርበታል።

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ለጀፎረ ባህላዊ መንደር ልዩ ትኩረት ተስጥቷል። እንደ ሃገር የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ ደግሞ የጉራጌ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ የአኗኗር ፍልስፍና የሆነውን ጀፎረን ወጥ በሆነ መልኩ ለማልማት እያስቻለ ነው። ይህም እሴቱን አጠናክሮ ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገርና የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ ሚናው የጎላ ነው።

በጉራጌ ዞን የጌታ ወረዳ ነዋሪ አቶ ፈቀደ አለማር እንደሚሉት በጀፎረ መንደር ቤቶች በልዩ ውበት እና በተቀናጀ ሁኔታ ነው የሚገነቡት። ቤቶቹ ከመንገድ ዳርና ዳር ተርታ የሚገነቡ ሲሆን በቤቶቹ መካከል ያለው ሰፊ መንገድም በአረንጓዴ ሣር የተሸፈነ ነው። በአረንጓዴ የተሸፈነው መንገድ ግራና ቀኝ ተርታውን ተሰልፈው ከሚታዩ ጎጆ ቤቶችና በእኩል ቁመት ከታጠረው የእንጨት አጥርና የእንሰት ተክል ጋር ተዳምሮ ሲታይ ለአካባቢው እንዳች ውበት ይሰጣል። 

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ መንግስት ለጉራጌ የጀፎረ መንደር አመሰራረት ትኩረት መስጠቱ በተሻለና በዘመነ መልኩ እሴቱን ለማስቀጠል እያገዘ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን አቶ ፈቀደ ይናገራሉ። ይህም መንደሩን ይበልጥ በማዘመን ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል ብለዋል።

የእዚሁ ወረዳ ሌላው ነዋሪ ወይዘሮ ደስታ አንሳ ጀፎረ የደስታና የሀዘን መገለጫ ማዕከል ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ያነሳሉ። በተለይ እንደ መስቀል በዓል ባሉ ታላላቅ በዓላት ጀፎረ የባህላዊ ጨዋታዎችና ዘፈኖች መድረክ ሆኖም እንደሚያገለግል ነው የገለጹት።

ወጣቶችና አዛውንቶች ተሰባስበው ደስታቸውን የሚገልጹበት እንደ ሠርግና ሀዘን ባሉ ማህበራዊ ጉዳዮችም አብሮነታቸውን የሚያሳዩበት ህያው ቦታ መሆኑንም ነው ያነሱት።

"ጀፎረ" የግጭት መፍቻና የዕርቅ ማዕከልም ሆኖ ያገለግላል። በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ማናቸውም አለመግባባቶች ወደ ውጭ ሳይወጡ በጀፎረ መንደር በሽማግሌዎች ይፈታሉ የሚሉት ደግሞ የእኖር ወረዳ ነዋሪው የሃገር ሽማግሌ ጓታኩየ መልስ ናቸው።

የዳኝነት ሥርዓቱ ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰባዊ ሰላምን የሚጠብቅ በመሆኑ፣ በ"ጀፎረ" የሚተላለፉ ውሳኔዎች ከፍተኛ ክብር እና ተቀባይነት እንዳላቸው ያነሳሉ።

"ጀፎረ" የጉራጌ ማህበረሰብ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን አስተሳስረው የሚመሩበት ለዘመናት የዘለቀ ድንቅ እሴት መሆኑን ያወሱት ደግሞ የጉራጌ ዞን ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ተወካይ አቶ ነስረዲን አረቦ ናቸው። እሴቱ ማህብረሰቡን የማስተሳሰር፣ ግጭትን በዘላቂነት መፍታት፣ ሰላምና ልማትን እንደሚሰብክ ተናግረዋል።

በመሆኑም በማህብረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ተቀባይነት ያለው እሴቱ ሳይሸራረፍ ተጠብቆ መቆየቱን አስረድዋል። እንደ አቶ ነስረዲን ገለጻ፤ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ባህላዊው የ”ጀፎረ” አቀማመጥ ከዘመናዊው የኮሪደር ልማት ጽንሰሀሳብ ጋር በማጣጣም እየተተገበረ ይገኛል።

ሰፋፊ ጎዳናዎች አረንጓዴ ማነታቸው ተጠብቆ በዘላቂነት እንዲጠበቁ ለማድረግ ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር ተሰናስኖ እየተተገበረ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ ህብረተሰቡን በማሳተፍ መሰራቱን አስረድተዋል።

በተያዘው በጀት አመትም በሩብ አመቱ ከ85 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነውን የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል።

በዘርፉ ልዩ እቅድ ተይዞ በተሰራው ሰራ አራት ጀፎሮዎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደተሰራላቸው ገልፀው በቀጣይ 12 ቦታዎች ተለይተው የይዞታ መሳረጋገጫ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ነስረዲን ገለጻ “ጀፎረ” ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ በማድረግ የጉራጌን ታሪክ፣ ባህልና መስተንግዶ ለውጭ ሀገርና ለሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ለማስተዋወቅ በተሰራው ስራ ውጤቶች እየተገኙ ነው።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም