ቀጥታ፡

በመቀሌ ከተማ የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል - ሺሻይ አማረ (ዶ/ር)

መቀሌ፤ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፦ በመቀሌ ከተማ ባለፉት 30 ቀናት ሰላምን በማስፈን፣ መንግሥታዊ ተቋማትን እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን ወደ መደበኛ ሥራ በመመለስ ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን በትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ሽሻይ አማረ(ዶ/ር) ገለጹ።

ከንቲባ ሹሻይ አማረ (ዶ/ር) ከተማ አስተዳደሩ ባለፈው አንድ ወር ያከናወናቸውን እና በቀጣይ የሚሰሩ የሥራ እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል ።

ከንቲባው በመግለጫቸው እንዳሉት ባለአደራ አስተዳደሩ በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት የህዝብን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ስራ እያከናወነ ነው።

በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በሰላምና መረጋጋት ማስፈን፣ የመንግሥት መዋቅርን መልሶ በማደራጀትና የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ አወንታዊና ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የገበያ ሁኔታን ለማረጋጋትና የሸቀጦች አቅርቦትን ለማሻሻል እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማነቃቃት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

በትራንስፖርት ዘርፍ እንዲሁም ህገወጥ ተግባራትን በመከላከልና ህግን በማስከበር ብሎም ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

በትምህርትና ጤና አገልግሎቶች ተጨባጭ ለውጥ እየታየ መሆኑንም አክለዋል።

በቀጣይ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ለማስጀመርና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ ህዝብን ያሳተፈ የውይይትና የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ጨምረው አመልክተዋል።

አሁን ላይ ለወጣቶች ስራ ለመፍጠር ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።

የከተማዋን የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ ማሻሻል፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን ማስቀጠልና የከተማዋን የልማት እንቅስቃሴ ማጠናከር ከቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች መካከል እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።

ባለአደራ አስተዳደሩ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ስኬታማነት መላው ህብረተሰብና ባለድርሻ አካላት የጀመሩትን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም