ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢትዮጵያን ተመራጭ የንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከል እያደረጋት ነው - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፦የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢትዮጵያን ተመራጭ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ ማዕከል እያደረጋት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ካውንስል (CFR) ፕሬዚዳንትና የልዑካኑ መሪ ማይክል ፍሮማን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሥርዓት አስደናቂ ዕድገት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ ከአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ካውንስል (CFR) ልዑካን ቡድን አባላት ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

ውይይታቸው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ በቀጣናዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መስኮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተወያየው ልዑካን ቡድንም የአሜሪካ ተቋማትን የመሩ፣ የኢንቨስትመንት አማካሪዎችና አልሚ ባለሀብቶችን ያካተተው መሆኑ ተመላክቷል።

የገንዘብ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዝግጁነትና አማራጮች ለመመልከት መምጣቱን ገልጸዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት እያደረገቻቸው ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ፍላጎት እየፈጠሩ መምጣታቸውን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያም በርካታ የአሜሪካ አልሚ ባለሀብቶች ፍላጎት እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም የአሜሪካ አልሚዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለመግባት የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እየተመለከቱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የበለጠ ምቹ፣ ዝግጁና ሳቢ እየሆነች መምጣቷን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ልዑካን ቡድኑ በሚመለስበት ወቅትም በኢትዮጵያ ባሉ መልካም ዕድሎች ላይ ግንዛቤ በመስጠት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ልዑኩ በቆይታው በመሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ተዘዋውሮ እንደሚመለከትና የተሻለ ኢንቨስትመንትን ያመጣል ተብሎ እንደሚታሰብ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ካውንስል (CFR) ልዑክ በተለያዩ ጊዜያት የአሜሪካ ተቋማትን የመሩ ሰዎችን ያካተተ ነው ብለዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላትም የኢትዮጵያን አጠቃላይ የልማት፣ የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ዕድገቶችን ለመመልከት መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በውይይታቸውም በአጠቃላይ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ገልጸው፣ ልዑኩ በኢትዮጵያ የተከናወነው የኢኮኖሚ ሪፎርም ባስገኘው ውጤት መደነቃቸውን አንስተዋል።

በቀጣይም ልዑኩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው እንደሚጎበኙ ገልጸው፣ የኢትዮጵያና የአሜሪካን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ትርጉም ያለው ውይይት እንደነበር ጠቁመዋል።

ከአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ካውንስል (CFR) ፕሬዚዳንትና የልዑካኑ መሪ ማይክል ፍሮማን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የንግድ፣ ኢንቨስትመንት አማራጮችና የሁለት አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር ጠቃሚ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያን መልካም የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን በጥልቀት መመልከት ያስቻለ ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸው፤ በዚህም የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሥርዓት አስደናቂ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን እንደተገነዘቡ አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም