ቀጥታ፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የተከልናቸው ችግኞች ለገቢ ምንጭነት እያገለገሉን ነው- ተቋማት እና አርሶ አደሮች

ጂንካ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)  በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የተከሏቸው የፍራፍሬ ችግኞች ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ለተጨማሪ የገቢ ምንጭነት እያገለገሏቸው መሆኑን በአሪ ዞን የሚገኙ ተቋማት እና አርሶ አደሮች ገለፁ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከስምንት ዓመታት በፊት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር  ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።

በአመታቱ ያለማቋረጥ በመርሐ ግብሩ ከተሳተፉ ቋማት መካከል የጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተጠቃሽ ሲሆን የኮሌጁ ምክትል ዲን ተመስገን ኢሳያስ አረንጓዴ አሻራ በርካታ ውጤቶች ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

ኮሌጁ ምርታማነትን በእጥፍ የሚያሳድጉና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን የአቮካዶ፣ የፓፓያ፣ የሙዝና የማንጎ እና  ዝርያዎችን በመትከልና በማስፋፋት ለማህበረሰቡ ጭምር በማሰራጨት ለመርሐ ግብሩ ስኬት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

በኮሌጁ ተተክለው እየለሙ ያሉ  የአቮካዶና ሌሎች የፍራፍሬ ዝርያዎች በአጭር ጊዜ በእጥፍ ምርት የሚሰጡ የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

 የፍራፍሬ ተክሎቹ ለኮሌጁ ምቹ የመማሪያ አካባቢ ከመፍጠር ባለፈ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

 በአሪ ዞን የባካዳውላ አሪ ወረዳ የአርክሻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገበየሁ ቃቆ በበኩላቸው አካባቢው ተዳፋት በመሆኑ ለጎርፍና ለናዳ ተጋላጭ እንደነበር አስታውሰው ባለፉት አመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ  ችግኝ ተከላ ተጋላጭነቱ በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል ።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቡና፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ እና ሙዝ በማልማት ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልፀው ተክሎቹ ምርት በመስጠት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል ።

ሌላዋ የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር አስቴር በርቂ በበኩላቸው አካባቢው በተራራ የተከበበና ለጎርፍ ተጋላጭ መሆኑን ተናግረዋል ።

 ይሁንና  በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመስራት የተለያዩ ችግኞችን በመትከል ማልማት እንደተቻለ ገልጸዋል።

ሞሪንጋ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያና ሙዝ የመሳሰሉ ተክሎችን በማልማት ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆኑን አመልክተዋል ።

የአሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ በአሪ ዞን የአረንጓዴ አሻራ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ተጨባጭ ለውጦች  መታየታቸውን ገልጸዋል ።

በዞኑ የደን ሽፋን እያደገ መምጣቱንና የተራቆቱ አካባቢዎች ጭምር አገግመው ምርት መስጠት መጀመራቸውን ጠቅሰው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከአካባቢ ጥበቃነቱ ባሻገር ለስራ እድል ፈጠራና ለገቢ ምንጭ እያገዘ መሆኑን አስታውቀዋል 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም