የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ክፍት በማድረግ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ክፍት በማድረግ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ክፍት በማድረግ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን የፈርስት ኢንዲፔንደንስ ባንክ ሊቀ መንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኬኒት ኬሊ ገለጹ።
ኬኒት ኬሊ የፈርስት ኢንዲፔንደንስ ባንክ ሊቀ መንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የአሜሪካ ባንክ ባለሙያዎች ማኅበር ሊቀ መንበር ናቸው።
ሊቀ መንበሩ በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ (ፊንቴክ)፣ ማይክሮ ፋይናንስና ቴሌኮም ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ባንኮች አቅምና ተያያዥ ጉዳዮች ተወያይተዋል።
በውይይቱም በአሜሪካ የኢንቨስትመንት ባንኮች የቴክኖሎጂ አቅምና አጠቃቀም እንዲሁም በፊንቴክና ቴሌኮም ዘርፎች ዝግጁነት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የባንክና የፋይናንስ ኢንዱስትሪ አዳጊ መሆኑንና ለኢኮኖሚ መዘመን አቅም የሚሆን ለውጥ እየታየ መምጣቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ለልማት ክፍት በማድረግ የውጭ ባንኮች ኢንቨስት የሚያደርጉበትን ወሳኝ ዕድል የፈጠረ ታላቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
ከፊንቴክ፣ማይክሮ ፋይናንስና ቴሌኮም ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ያደረጉት ውይይት አነስተኛ ቢዝነሶችን በማጠናከር ኢኮኖሚውን ማሳደግ የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠሩንም አመልክተዋል።
በቀጣይም የአሜሪካ ኩባንያዎች አነስተኛና ማይክሮ ፋይናንስ አንቀሳቃሾችንና ሌሎች ዘርፎችን በመደገፍ አቅማቸውን ለማጠናከር እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።
የባንክ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት መደረጉን፣ ቀጣይነት ያለው ሪፎርም እየተካሄደ መሆኑንና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በፍጥነት እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።
የፊንቴክና የማይክሮ ፋይናንስ ዕድገት ውድድርን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፤ የፋይናንስ ዘርፉ ተደራሽነት ኢንቨስትመንትን እንደሚስብ ገልጸዋል።