የኢትዮጵያን ብዝኅ ጸጋና ዘመን አይሽሬ ታሪክ- የሀገሬ ስጦታ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብዝኅ ጸጋና ዘመን አይሽሬ ታሪክ- የሀገሬ ስጦታ
በቁምልኝ አያሌው!
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
በዘመናችን የአየር ንብረት ለውጥ የሰው ልጆችን ሕልውና፣ የሥነ-ምህዳር ሚዛንና የዓለምን ዘላቂነት በእጅጉ እየተፈታተነ ይገኛል። እርሱ እያስከተለ ያለው ዳፋ የሀገራትን ሉዓላዊ ወሰን ሳይበግር፣ የውቅያኖሶችንና የባሕር ወለል ስፋት ሳይገድብ በሁሉም ዘንድ ደራሽ ሆኖ ቀጥሏል። ከኢንዱስትሪ አብዮት ማግስት ጀምሮ የሰው ልጅ ያልተገራ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ምድር መሸከም ከማትችለው ማጥ ውስጥ እየከተታት መጥቷል። የሥነ-ምኅዳር መጎሳቆል፣ የነዳጅ አጠቃቀም፣ የኢንዱስትሪ በካይ ጋዝ ልቀት እና የግሪን ሐውስ ጋዞች መጨመር የአየር ንብረት ለውጥ መሠረታዊ ምክንያቶች ናቸው። የምድር አማካይ ሙቀት መጨመርም የዚህ ለውጥ አንዱ ዋነኛ መገለጫ ነው። የከፋ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የሙቀት ማዕበል፣ የውኃ እጥረት፣ የብዝኅ ሕይወት መመናመንና የምግብ ዋስትና መናጋት ተደራራቢ ተጽዕኖዎች እየሆኑ መጥተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ አሳሳቢነት በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ፍትሐዊነት፣ በሕዝብ ጤና፣ በሰላምና በዓለም አቀፍ ደኅንነት ላይ ጎልቶ እየታየ ነው። በተለይም ቀውሱ ወሰን የለሽ ቢሆንም፣ የግሪን ሐውስ ጋዝ ልቀት አነስተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የአህጉራችን አፍሪካና የሌሎች ታዳጊ ሀገራት ማኅበረሰቦች የዳፋው ከፍተኛ ሰለባ ናቸው።
ይህም የአየር ንብረት ለውጥን ከሳይንሳዊና አካባቢያዊ ጉዳይነት ባሻገር የፍትሐዊነት፣ የታሪካዊ ኃላፊነትና የዓለም አቀፍ አብሮነት ጥያቄ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህም የሀገራትን የልማት ፍላጎት፣ የልቀት ቅነሳ ግዴታና የማኅበረሰቦችን የመላመድ አቅም በሚዛናዊነት ማገናዘብ ወሳኝ ነው።
የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ መድረክ፡ ማን? መቼ አስተናገደ?
በዚህ ዓለም አቀፍ ፈተና ዙሪያ የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት (UNFCCC) የተሳታፊ ሀገራት ጉባኤዎች የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲና የፖሊሲ ውይይት ዋነኛ መድረኮች ናቸው። እነዚህ መድረኮች የሀገራትን የልቀት ቅነሳ ቃል ኪዳኖች፣ የአየር ንብረት ለውጥ መላመድ ስልቶች፣ የፋይናንስ ድጋፍ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኪሳራና ጉዳት ጉዳዮችን በጋራ የሚመክሩባቸውና ስምምነቶች የሚደረሱባቸው ወሳኝ ማዕቀፎች ናቸው።
የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ መድረኮች በሳይንሳዊ ምርምር፣ በዓለም አቀፍ ውይይትና በሕጋዊ ስምምነቶች የተገነባ ረጅም ሂደት አልፈዋል። ከ1979 እስከ 2026 በተለያዩ ሀገራት የተካሄዱት ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መድረኮችና ጉባኤዎች የሂደቱን ታሪካዊ የጉዞ ምዕራፎች ያመላክታሉ።
በዚህም እ.ኤ.አ. በ1979 በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ የተካሄደው የመጀመሪያው የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (First World Climate Conference) ሳይንሳዊ ግንዛቤን ለማሳደግ መሠረት ጥሏል፤ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ1988 በጄኔቫ የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተጠሪ ቡድን (IPCC) መመሥረቱ ዓለም አቀፍ ሳይንሳዊና ተቋማዊ መሠረት የፈጠሩ ናቸው። እነዚህ ሁለቱም ከUNFCCC እና ከCOP ጉባኤዎች ቀደም ብለው የተከናወኑ ታሪካዊ የሆኑ ሳይንሳዊና ተቋማዊ ምዕራፎች ናቸው።
በመቀጠልም የኮፕ (COP) ጉባኤዎች ሂደት በብራዚሏ ሪዮ ዴ ጄኔሮ (እ.ኤ.አ. 1992 የምድር ጉባኤ/UNFCCC መፈረሚያ)፣ በጀርመን በርሊን (COP 1፣ 1995)፣ በጃፓን ኪዮቶ (COP 3፣ 1997)፣ በሞሮኮ ማራካሽ (COP 7፣ 2001)፣ በዴንማርክ ኮፐንሃገን (COP 15፣ 2009)፣ በፈረንሳይ ፓሪስ (COP 21፣ 2015)፣ በዩናይትድ ኪንግደም ግላስጎው (COP 26፣ 2021)፣ በግብፅ ሻርም ኤል ሼክ (COP 27፣ 2022)፣ በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ዱባይ (COP 28፣ 2023)፣ በአዘርባጃን ባኩ (COP 29፣ 2024) እንዲሁም በብራዚል ቤለም (COP 30፣ 2025) በመካሄድ በርካታ የታሪክ ሂደቶችን አሳልፏል።
31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 31) በቱርኪዬ አስተናጋጅነት በአንታሊያ እየተካሄደ ነው። ኢትዮጵያም በ2027 በአዲስ አበባ 32ኛውን የስምምነት ወገኖች ጉባኤ (COP 32) ለማስተናገድ የቅብብሎሽ ዝግጅቷንና የአፍሪካ ቡድን ድጋፍን በማጠናከር በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።
የኮፕ (COP) መድረክ አስተናጋጅ ሀገራት፡ የመሪነት፣ የብሔራዊ ገጽታ ግንባታና የብራንድ ስትራቴጂክ ትርጓሜ
የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ የተሳታፊ ሀገራት ጉባኤዎች (COP) አስተናጋጅነት ከአንድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ መስተንግዶ በላይ ቁልፍ የሆነ የዲፕሎማሲ፣ የስትራቴጂክ ግንኙነት፣ የብሔራዊ ገጽታ ግንባታና የዓለም አቀፍ ተሰሚነት ማሳደጊያ መድረክ ነው። ሀገራትም ይህንን አጋጣሚ የብሔራዊ ማንነታቸውን፣ የባህል ሀብታቸውን፣ የልማት ርዕያቸውንና የአካባቢ ጥበቃ ቁርጠኝነታቸውን ለዓለም ለማስተዋወቅ ተጠቅመውበታል።
የአስተናጋጅ ሀገር መሪ የሚያሳየው የዲፕሎማሲ አቅጣጫ፣ የጉባኤው ፕሬዝዳንት የሚወስደው የድርድር አመራር፣ የሀገር ይፋዊ መልዕክት፣ የጉባኤው ሎጎ (LOGO)፣ የቀለም ምርጫ፣ የምልክት አጠቃቀምና የመድረኩ አጠቃላይ የዕይታ አቀራረብ የሀገርን ምስል በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።
በዚህም የCOP ጉባኤ ከዓለም አቀፍ የፖሊሲ ድርድር መድረክ ባሻገር ሀገራት የራሳቸውን ብሔራዊ ትርክት (National Narrative) ለዓለም የሚያስተዋውቁበት የስትራቴጂክ ገጽታ ግንባታና የብራንዲንግ መድረክ ወደ መሆን ተሸጋግሯል። ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤዎችን ያስተናገዱ ሀገራት በሎጎ እና በብራንድ ዐሻራዎች ምን አተረፉበት የሚለውን እንደሚከተለው በወፍ በረር እንቃኝ፤ የኢትዮጵያ ዝግጅትና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአንታሊያ ስጦታስ ምንድን ነው?
የሀገራት የCOP አስተናጋጅነትና የብሔራዊ ገጽታ ግንባታ ዝግጅትና አቀራረብ
የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤዎች አስተናጋጅ ሀገራት የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ድርድርን ከማስተናገድ ባሻገር፣ ታሪካዊ ማንነታቸውን፣ ባህላዊ እሴቶቻቸውን፣ ተፈጥሯዊ ሀብታቸውንና የዲፕሎማሲ አቅማቸውን ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያገለግል መድረክ አድርገው ተጠቅመውበታል። የጉባኤዎቹ ሎጎዎች፣ የቀለም ምርጫዎች፣ የምስል ቋንቋዎች፣ የመሪዎች አቀራረብና የመገናኛ ብዙሃን ሥራ የብሔራዊ ገጽታ ግንባታ አካላት ናቸው።
ፈረንሳይ - ፓሪስ (COP 21፣ 2015) ፈረንሳይ በCOP 21 ጉባኤ ሀገራዊ ብራንዷን ለማስተዋወቅ የሀገሪቱን መታወቂያና መገለጫ የሆነውን የኤፍል ታወር (Eiffel Tower) ከተፈጥሮ ምልክት ከሆነው የዛፍ ቅጠል ጋር አሰናስሎ የያዘ ሎጎ ተጠቅማለች። የጉባኤው ሎጎ በቅጠል ቅርጽ የተነደፈ ሲሆን፤ በውስጡ የኤፍል ታወር ምስልን አካትቷል። አረንጓዴው ቀለም ከተፈጥሮና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ሲያያዝ፣ የኤፍል ታወር ምስል ደግሞ የፓሪስንና የፈረንሳይን ዓለም አቀፍ መለያነት አጉልቶ አሳይቷል።
የፈረንሳይ የዲፕሎማሲ አቀራረብ ዋነኛ ትኩረት ሀገራትን በአንድ የጋራ ስምምነት ማሰባሰብ ነበር። የዛን ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎራን ፋቢየስ (Laurent Fabius) የጉባኤውን ድርድር በመምራት የፓሪስ ስምምነት እንዲደረስ ቁልፍ የዲፕሎማሲ ሚና ተጫውተዋል። ይህም ፈረንሳይን በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ አድርጎ አቅርቧታል።
ሞሮኮ - ማራካሽ (COP 22፣ 2016) ሞሮኮ የCOP 22 ጉባኤን በማራካሽ በማስተናገድ የሀገሪቱን ታሪካዊና የሥነ-ጥበብ ማንነት ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት አጀንዳ ጋር አጣምራ አቅርባለች። የጉባኤው ሎጎ በማራካሽ የሚገኘውን ታሪካዊ የመናራ (Menara) ሕንፃ ከሞሮኮ ባህላዊ የዚሊጅ (Zellige) ሞዛይክ ጌጣጌጥ ጋር አጣምሮ የተነደፈ ነበር። የመናራ ምስል ከታሪካዊ የውኃ አስተዳደር ሥርዓት ጋር የተያያዘ መሆኑም የውኃ ሀብትን በዘላቂነት የመጠቀም መልዕክትን አጉልቶ አሳይቷል።
የሞሮኮ የብራንድ ስትራቴጂም የሀገሪቱን ባህላዊ ሀብት በዘመናዊ የዓለም አቀፍ ጉባኤ ማንነት ውስጥ ማካተት ነበር። በዲፕሎማሲው በኩልም የአፍሪካና የታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ፍትሕ፣ የፋይናንስ ድጋፍና የተግባር ማስፈጸሚያ ጥያቄዎችን አጉልታ አቅርባለች።
ፊጂ - COP 23 (2017)፤ ተካሄደ በጀርመን ቦን ከተማ ፊጂ (Fiji) በደቡብ ፓሲፊክ ውቅያኖስ የምትገኝ ሉዓላዊ የደሴት ሀገር ናት። ፊጂ በ2017 የCOP 23 ፕሬዝዳንትነትን ብትመራም ጉባኤውን በሀገሯ ለማስተናገድ በቂ የሎጂስቲክስ አቅም ባለመኖሩ ከጀርመን መንግሥት ጋር በመተባበር በቦን ከተማ እንዲካሄድ አድርጋለች።
የጉባኤው ሎጎ በውኃ ውስጥ በከፊል የሰመጠች ደሴትንና ወደ ደሴቷ እየተጠጋ ያለ ማዕበልን የሚያሳይ ነበር። ይህ ምስል በተለይ በትንንሽ ደሴት ሀገራት ላይ የባሕር ወለል ከፍታ መጨመርና የከባድ አውሎ ነፋሶች መበርታት የሚያስከትሉትን አደጋ አጉልቶ አሳይቷል።
ፊጂ የሎጎውን ዲዛይን በሀገራዊ የውድድር ሂደት መርጣ ለሕዝብ ተሳትፎ ቦታ በመስጠት ማዘጋጀቷን መረጃዎች ያመላክታሉ። የዚያን ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንክ ባይኒማራማ (Frank Bainimarama) የጉባኤውን ፕሬዝዳንትነት በመያዝ የተጋላጭ ደሴት ሀገራት ድምፅ በዓለም ድርድር ላይ እንዲሰማ አድርገዋል። ይህም የፊጂን ብራንድ ከደሴታዊ ማንነትና ከአየር ንብረት ፍትሕ ጥያቄ ጋር አቆራኝቶ አሳይቷል።
ፖላንድ - ካቶቪስ (COP 24፣ 2018) ፖላንድ የCOP 24 ጉባኤን በካቶቪስ ከተማ በማስተናገድ የሀገሪቱን ብሔራዊ ምልክትና የከተማዋን የአካባቢ መለያ በአንድ የዕይታ ቋንቋ ማቅረብ ችላለች። የጉባኤው ሎጎ የፖላንድን ካርታ የሚያስታውስ ሰማያዊና አረንጓዴ ቅርጽ እንዲሁም የካቶቪስ ከተማን የሚወክል ባለቀለም የልብ ቅርጽ አካትቷል።
የዚህ የብራንድ አቀራረብ ዋነኛ ጥቅም ብሔራዊና አካባቢያዊ ማንነትን አንድ ላይ ማሳየቱ ነው። ካቶቪስ በከሰል ኢንዱስትሪና በከባድ ኢንዱስትሪ ታሪኳ የምትታወቅ ከተማ መሆኗ የጉባኤውን የኃይል ሽግግርና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ውይይት በተለየ አካባቢያዊ ትርጉም አሰጥቶታል።
ቺሊ - COP 25 (2019)፤ ተካሄደ በስፔን ማድሪድ ከተማ ቺሊ በ2019 የCOP 25 ጉባኤን ለማስተናገድ ቁርጠኝነቷን ብታሳይም በሀገሪቷ በተቀሰቀሰው ማኅበራዊ ዓመፅና የደኅንነት ቀውስ ምክንያት ጉባኤውን በሳንቲያጎ ማካሄድ ባለመቻሏ አስተናጋጅነቱን ለመተው ተገዳለች።
በዚህም የጉባኤውን መስተንግዶ ስፔን በማድሪድ ከተማ አስተናግዳለች፤ ቺሊ ደግሞ የጉባኤውን ፕሬዝዳንትነትና የድርድር አመራሩን ይዛ ቀጥላለች። የጉባኤው የብራንድ ማንነትም በቺሊ ቅርጽና ርዕይ የተመሠረተ ነበር።
የCOP 25 ሎጎ በአብዛኛው ሰማያዊ ቀለም የተጠቀመ ሲሆን፤ ውቅያኖስን፣ ባሕርን፣ ንጹሕና ታዳሽ ኃይልን እንዲሁም የአየር ንብረት እርምጃ አጣዳፊነትን ያመለክታል። በሎጎው ውስጥ የሰዓት ምልክት መካተቱ “የእርምጃ ጊዜው አሁን ነው” የሚል መልዕክት አስተላልፏል። የቺሊ ረጅምና ጠባብ የመሬት ቅርጽም በሰዓቱ ውስጥ እንደ ሀገሪቷ መለያ ተካትቷል። ይህ የብራንድ አቀራረብ የቺሊን ረጅም የባሕር ዳርቻ፣ የባሕር ሥነ-ምህዳር ጥበቃና የንጹሕ ኃይል አቅጣጫ በአንድ የዕይታ መልዕክት አጣምሮ ይዟል።
ዩናይትድ ኪንግደም - ግላስጎው (COP 26፣ 2021) ዩናይትድ ኪንግደም የCOP 26 ጉባኤን በስኮትላንድ ግላስጎው ከተማ በማስተናገድ የዓለምን የጋራ የአየር ንብረት እጣ ፈንታ የሚወክል የዕይታ ቋንቋ አቅርባለች። የጉባኤው ሎጎ በአረንጓዴ፣ ሰማያዊና ነጭ ቀለሞች የተሠራ የሚዞር የምድርን ክብ ምስል ያካተተ ነበር። የአህጉራትን ቅርጽ በተለመደው መልኩ ከማሳየት ይልቅ በተዋሃደ የምስል ቅርጽ ማቅረቡ የአየር ንብረት ቀውስ የሁሉንም ሀገራት የጋራ ችግር መሆኑን አመላክቷል።
የጉባኤው ብራንድ ዋነኛ መልዕክት ተስፋን ከአጣዳፊ እርምጃ ጥሪ ጋር ያሰናሰለ ነበር። የወቅቱ የCOP 26 ፕሬዝዳንት አሎክ ሻርማ (Alok Sharma) የዓለም መሪዎች የፓሪስ ስምምነትን የሚያስፈጽሙ ቃል ኪዳኖችን እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል። ጉባኤው የግላስጎው የአየር ንብረት ስምምነት (Glasgow Climate Pact) እንዲወጣ መሠረት ጥሏል።
ግብፅ - ሻርም ኤል ሼክ (COP 27፣ 2022) ግብፅ የአፍሪካንና የጥንታዊ ግብፅን ታሪካዊ ማንነት ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ትርክት ጋር አጣምራ አቅርባለች። በግብፅ ደቡባዊ የሲናይ ባሕረ ገብ መሬት የቀይ ባሕር ዳርቻ በምትገኘው ሻርም ኤል ሼክ የተካሄደው የጉባኤው ሎጎ የአፍሪካን ፀሐይ፣ የጥንታዊውን የአቴን (Aten) የፀሐይ ምልክትና አዲስ አድማስን ያካተተ ነበር። የፀሐይ ጨረሮቹ የሕይወትንና የተፈጥሮን ለጋስነት ሲወክሉ፣ አዲሱ አድማስ የተሻለ የወደፊት ተስፋን ያመለክታል። በሎጎው ውስጥ ያለው የዓለም ክብ ወደ አፍሪካ የተመለከተ መሆኑም የአህጉሪቷን ማንነት አጉልቶ አሳይቷል።
የግብፅ የአስተናጋጅነት ዋነኛ የዲፕሎማሲ መልዕክት የአፍሪካን የአየር ንብረት ፍትሕ ጥያቄ ወደ ዓለም አቀፍ የድርድር ማዕከል ማምጣት ነበር። በተለይም የኪሳራና ጉዳት ፈንድ (Loss and Damage Fund) መመሥረት የጉባኤው ዋነኛ ውጤት ሆኗል።
የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች - ዱባይ (COP 28፣ 2023) ኤሚሬቶች የጉባኤውን ብራንድ በ“አንድ ዓለም” (One World) ጽንሰ-ሐሳብ ላይ መሥርተውታል። በክብ ቅርጽ የተቀረጸው ሎጎ ሰዎችን፣ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎችን፣ የዱር እንስሳትንና ተፈጥሮን በአንድ የዓለም ምስል ውስጥ አሰናስሎ የያዘ ነው። የአረንጓዴ ቀለም ምርጫውም ከዘላቂነትና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዘ የዕይታ መልዕክት ይፈጥራል።
የኤሚሬቶች መልዕክት የሰሜኑንና የደቡቡን ዓለም፣ የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ፣ ሳይንቲስቶችንና ማኅበረሰቡን በአንድ የጋራ እርምጃ ማሰባሰብ ነበር። የጉባኤው ፕሬዝዳንት ሱልጣን አል ጃበር (Sultan Al Jaber) ጉባኤው “አካታች እና ተግባር ተኮር” እንዲሆን በማስቀመጥ ከቃል ኪዳን ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚያሸጋግር አቅጣጫ አቅርበዋል።
አዘርባጃን - ባኩ (COP 29፣ 2024) አዘርባጃን የባህላዊ ማንነቷን የሚወክለውን የቡታ (Buta) ምልክት ከቅጠልና ከውኃ ጠብታ ምስሎች ጋር በማቀናጀት የጉባኤውን ሎጎ ነድፋለች። ምልክቱ ተፈጥሮን፣ ውኃን፣ አየርን፣ ኃይልንና የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ትስስር ይወክላል። የሎጎው ክብ ቅርጽ አንድነትንና የጋራ ኃላፊነትን ያመለክታል።
የአዘርባጃን የብራንድ ስትራቴጂ ባህላዊ ምልክትን ከዘመናዊ የአካባቢ ጥበቃ መልዕክት ጋር በማዋሃድ የሀገሪቱን ማንነት አጉልቶ አሳይቷል። በዲፕሎማሲም የአየር ንብረት ፋይናንስን ዋነኛ የድርድር አጀንዳ አድርጋ አቅርባለች፤ የCOP 29 ተሳታፊ ሀገራትም አዲስ የጋራ የቁጥር ግብ የአየር ንብረት ፋይናንስ ስምምነት (NCQG) ላይ መድረሳቸው የጉባኤው ዋነኛ ውጤት ሆኗል።
ብራዚል - ቤለም (COP 30፣ 2025) ብራዚል በሰሜናዊ የሀገሪቷ የአማዞን ክልል ቤለም ከተማ ያስተናገደችውን ጉባኤ ከአማዞን ደን፣ ከተፈጥሮ ብዝኅነትና ሀገር በቀል ማኅበረሰቦች ታሪክ ጋር አቆራኝታ አቅርባለች። “COP 30 Brasil Amazônia Belém 2025” የሚለው የብራንድ መለያ የአማዞንን ዓለም አቀፍ ሥነ-ምህዳራዊ ጠቀሜታና የብራዚልን ታሪካዊ ማንነት በአንድ የዕይታ ቋንቋ ያቀርባል። የቦታ ምርጫውም ከተለመዱት የዓለም አቀፍ ጉባኤ ማዕከላት በመውጣት በአማዞን ክልል የሚገኙ ማኅበረሰቦችንና የደን ጥበቃ ጥያቄን በዓለም መድረክ ላይ ለማጉላት ያለመ ነበር።
የCOP 30 ብራንድ በዋነኝነት የአማዞንን የተፈጥሮ ሀብት በምስልና በስም የሚያሳይ ሲሆን፤ በሰነዶችና በይፋዊ ግንኙነቶች ውስጥ የቅጠልና የተፈጥሮ ቅርጾችን የሚያስታውስ የዕይታ ማንነት ተጠቅሟል። ይህ አቀራረብ የአማዞንን ጉዳይ ከብራዚል ብሔራዊ ማንነት ጋር በማያያዝ የዓለም ትኩረትን ወደ ደን ጥበቃና የሥነ-ምህዳር ሚዛን መሳብ የሚያስችል ሐሳብን በማስተላለፍ ገጽታ ግንባታዋን አጉልቶ አሳይቷል።
ቱርኪዬ - አንታሊያ (COP 31፣ 2026)በደቡባዊ ቱርኪዬ የሜዲትራኒያን የባሕር ጠረፍ ከተማ በሆነችው አንታሊያ የ2026ቱ የCOP 31 ጉባኤ ተካሂዷል። ቱርኪዬ በአንታሊያ ያስተናገደችው መድረክ የሀገሪቷን የዲፕሎማሲ ታሪክ፣ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥና የአካባቢ ጥበቃ መልዕክት በአንድ የብራንድ ማንነት አጣምሮ አቅርቧል። የጉባኤው ሎጎ ሰማያዊ፣ አረንጓዴና ቀይ ቀለሞችን ያካተተ ክብ ቅርጽ ያለው ምልክት ሲሆን፤ ከ“COP 31 TÜRKİYE ANTALYA” የሚል ጽሑፍ ጋር ተያይዞ ቀርቧል። የሎጎው የተፈጥሮና የዓለም ክብ የሚያስታውስ ቅርጽ የጋራ ትብብርንና የዘላቂነት ግብን የሚያጎላ የዕይታ መልዕክት ይፈጥራል።
የቱርኪዬ የCOP 31 መሪ መልዕክት “ከውይይት ወደ ስምምነት፤ ከስምምነት ወደ ተግባር” የሚል የአቅጣጫ መልዕክት አስተላልፏል። በቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ሬጂፕ ጣይብ ኤርዶጋን አማካኝነት የCOP 31 ፕሬዝዳንትነት ሹመት የተሰጣቸው የቱርኪዬ የአካባቢ፣ የከተማ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ሙራት ኩሩም (Murat Kurum) ጉባኤው በውይይት፣ በመግባባትና በተግባራዊ ውጤት ላይ እንዲያተኩር አቅጣጫ በማስቀመጥ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።
የCOP 31 ብራንድ ከሎጎው ባሻገር የአንታሊያን የባሕርና የተፈጥሮ ሀብት ለማጉላት የባሕር ኤሊን (Caretta) እንደ ማስታወቂያ ምልክት ተጠቅሟል። ይህም የከተማዋን የባሕር ሥነ-ምህዳር ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ መልዕክት ጋር አሰናስሎ የተንጸባረቀበት መድረክ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ትጠብቃችኋለች፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአንታሊያ ስጦታ
ኢትዮጵያ የጥንት መነሻና የነገ ብሩህ ተስፋ የሚገናኙባት ምድር ናት። የኢትዮጵያ ታሪክ ከሰው ልጅ የቀደመ መገኛና ከቡና መፍለቂያነት ይጀምራል። ጥንታዊ የሥልጣኔ ሕያው ቅርሶቿ፣ አስደናቂ የተፈጥሮ ውበቶች፣ ስፖርታዊ ድሎች፣ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደም ሚና እና በማደግ ላይ የምትገኝ ሀገር ታላቅ ትልምና ርዕይ ያቅፋል። የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክና መነሻ ከነገ ጉዞዋና መዳረሻ ጋር የሚያስተሳስሩትን ሕዝቦች፣ ሥፍራዎችና ዕውቀቶች የሚያስቃኝ “ኢትዮጵያ - ምድረ ቀደምት” (Ethiopia - Land of Origins) የተሰኘ ብሔራዊ ድረ ገጽ (https://ethiopia.gov.et/am) ይፋ ሆኗል።
ምድረ ቀደምት ኢትዮጵያ የቀጣይን የ2027 ዓመት 32ኛ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP 32) በአዲስ አበባ በብቃት ለማስተናገድ ከወዲህ እየተዘጋጀች ነው። ጉባኤው የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ተሳትፎና ሚና የሚያጎላ ታሪካዊ መድረክ ይሆናል።
ለዚህም ነው እርስ በእርሱ የተሳሰረ አንደ ታሪክ የሚነግረንን ኢትዮጵያ የብሔራዊ ትዕምርት የሆኑትን የሰው ዘር መገኛ (Cradle of Humanity)፣ የቡና መገኛ (Origin of Coffee)፣ አረንጓዴ ዐሻራ (Green Legacy)፣ ጥንታዊ ሥልጣኔ (Ancient Civilization)፣ አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል (Diplomatic Hub)፣ የአሸናፊዎች ምድር (Land of Champions)፣ ንጹሕ ኃይል (Clean Energy) እንዲሁም የነገ ተስፋና የልማት ርዕይ (Future and National Ambition) ስምንት ዐበይት አምዶች ይፋ የተደረገው። ይህም ጉባኤው የኢትዮጵያን ገጽታ ግንባታ አጉልቶ ለማሳየት የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ቁርጠኝነት አንጓ ተደርጎ ይወሰዳል።
32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP 32) የኢትዮጵያና የሕዝቦቿን ታሪክ፣ ባህል፣ የአካባቢ ተግባራትና የወደፊት ርዕይ ለዓለም ለማስተዋወቅ ያላትን ዝግጅት ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡባዊ ቱርኪዬ የሜዲትራኒያን የባሕር ጠረፍ ከተማ በሆነችው አንታሊያ በተካሄደው የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ (COP 31) ከዓለም መሪዎች ጋር የዲፕሎማሲ ቆይታ አድርገዋል። ከጉባኤው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር ቆይታ አድርገዋል፤ ይህም የዘመናችን የጂኦ ፖለቲካና የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ አቀራረብ እየተቀየረ መምጣቱን ያመላክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንታሊያው ጉባኤ ያበረከቱት ስጦታ ምንድን ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቱርኪዬ በተካሄደው የCOP 31 ጉባኤ ለኢትዮጵያ ወዳጆች ያበረከቱት ስጦታ ትኩረትን ስቧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ትጠብቃችኋለች የሚል መልዕክትን የያዘ (“COP 32 Ethiopia — Await”)፣ ጥልቅ የሥነ-ጥበብ ገጽታ የተገለጠበትና ከዘንባባ የቅጠል ቅርጽ ጋር የተዋሃደ ስጦታ አበርክተዋል። ይህም ኢትዮጵያ ታላላቅ መድረኮችን በብራንዲንግና በምልክት ዲፕሎማሲ ለመጠቀም ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የሚያስተናግዱ ሀገራት ከመደበኛ የጠረጴዛ ላይ ምክክር መስተንግዶ ባሻገር የራሳቸውን ታሪክ፣ ባህል፣ ኢኮኖሚያዊ አቅምና ፖለቲካዊ ተሰሚነት የሚያስተዋውቁበት መድረክ እየፈጠሩ መጥተዋል። የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ ታሪካዊ ሽግግሮች የጉባኤ ሎጎ ዝግጅቶችን በቀላሉ እንደ ማስታወቂያ ምልክት ብቻ አልተጠቀሙባቸውም፤ በምትኩ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን፣ የተፈጥሮ ሀብታቸውንና የዲፕሎማሲ መልዕክታቸውን በማካተት ተጠቅመውባቸዋል። ኢትዮጵያም ለ2027ቱ መድረክ ከወዲሁ እየተዘጋጀች ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስጦታ ካበረከቱላቸው መሪዎች መካከል የቦትስዋና ፕሬዝዳንት ዱማ ጌዲዮን ቦኮ፣ የኳታር አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል-ታኒ፣ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆናስ ጋህር ስተር፣ የፊንላንድ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ስተብ፣ የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ እና ሌሎች መሪዎች ይገኙበታል። ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ትጠብቃችኋለች — “COP 32 Ethiopia — Await”፤ የኢትዮጵያን ብዝኅ ጸጋና ዘመን አይሽሬ ታሪክ በልብዎ ይቅረጹ!